የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትር በኪዬቭ ከፕሬዚዳንት ዜለንስኪ ጋር ተወያዩ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ወደ ዩክሬኗ መዲና ኪዬቭ አቅንተው ከፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜለንስኪ ጋር ተወያይተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝታቸው ለዩክሬን ህዝብ "የአብሮነትና አጋርነት ማሳያ" ነው ብለዋል።
ከስብሰባው በኋላ ዳውኒንግ ስትሪት ዩናይትድ ኪንግደም ዩክሬንን ለመደገፍ 120 የታጠቁ ተሽከርካሪዎችን እና ፀረ-መርከብ ሚሳኤሎችን እንደሚልክ ተናግሯል።
የዩክሬን ከፍተኛ ባለስልጣናት ዩናይትድ ኪንግደም ከሩሲያ ጋር ባለው ጦርነት ላደረገችው ድጋፍ አመስግነዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ጆንሰን የኪዬቭ ጉብኝት አስቀድሞ ያልተገለጸ ሲሆን በለንደን የሚገኘው የዩክሬን ኤምባሲ ከፕሬዚዳንት ዜለንስኪ ጋር የተገናኙበት ፎቶግራፍ በትዊተር ገጹ ላይ መለጠፉን ተከትሎ ነው የመሪው ጉብኝት የታወቀው።
የዳውኒንግ ስትሪት ቃል አቀባይ "ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለዩክሬን ህዝብ ያላቸውን አጋርነት ለማሳየት ከፕሬዝዳንት ዜለንስኪ ጋር በአካል ለመገናኘት ወደ ዩክሬን ተጉዘዋል።" ብሏል
ጠቅላይ ሚኒስትር ጆንሰን ከስብሰባው በኋላ በሰጡት መግለጫ "የዩክሬን ፕሬዚዳንት ዜለንስኪ ቆራጥ አመራር እና የዩክሬን ህዝብ የማይበገር ጀግንነት እና ድፍረት" አመስግነዋል።
ዩክሬን ባልተጠበቀ ሁኔታ የሩስያ ኃይሎችን ወደ ኪዬቭ እንዳይደርሱ አግተዋቸዋል ብሏል።
"በዚህ ቀጣይነት ባለው ጦርነት ዩናይትድ ኪንግደም ከጎናቸው እንደምትቆም ዛሬ ግልጽ አድርጌያለሁ፣ እስከ ዘለቄታቸው ከጎናችሁ ነን" ብለዋል።
አክለውም "ይህንን አሳዛኝ ክስተት ለማስወገድ የራሳችንን ወታደራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ድጋፍ እያጠናከርን እና ዓለም አቀፋዊ ጥምረት እየፈጠርን ነው፤ እናም ዩክሬን ነጻ እና ሉዓላዊ ሀገር ሆና እንድትቀጥል ማስቻል አለብን" ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ጆንሰን አገራቸው ዩናይትድ ኪንግደም 770 ሚሊዮን ፓውንድ የብድር ዋስትናዎች በማመቻቸት ተጨማሪ ኢኮኖሚያዊ ድጋፍን አረጋግጠዋል።
ከፕሬዚዳንት ዘሌንስኪ ጋር በቪዲዮ በሰጡት መግለጫ ጆንሰን እንዳሉት ዩክሬናውያን "የአንበሳ ድፍረት አሳይተዋል ነገር ግን አንተ ዜለንስኪ እንደ አንበሳው አስገምግመሃል" በማለት አሞካሽተዋቸዋል።
ዩናይትድ ኪንግደም እና ሌሎች ዩክሬንን የሚደግፉ ሀገራት የሩሲያ ሃይድሮካርበን መጠቀም ከማቆም ጀምሮ በሩሲያ ላይ የጣሉትን የኢኮኖሚ ማዕቀብ በቀጣይም አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጿል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም "ባለፉት ጥቂት ሰዓታት ውስጥ በጣም ውብ የሆነችውን ሀገርህን ለማየት ችያለሁ፤ እናም አስደናቂ ሀገር ነች። ጦርነቱ ያስከተለውን አሳዛኝ ውጤት ተመልክቻለሁ። በፍፁም ምክንያታዊ የሌለውና አላስፈላጊ የሆነ ጦርነት ነው" ብለዋል












