በደቡብ አፍሪካ የጣለው ከባድ ዝናብ ባስከተለው ጎርፍ ከ250 በላይ ሰዎች ሕይወት ማለፉ ተገለጸ

ታትሟል

በደቡብ አፍሪካ የወደብ ከተማ ደርባን አካባቢ በባህር ዳርቻ ላይ በደረሰው የጎርፍ አደጋ ከ250 በላይ ሰዎች ሕይወት ማለፉን ባለሥልጣናት አስታወቁ።

የኩዋዙሉ ናታል ጤና ጥበቃ ሚኒስትር ኖማጉጉ ሲሜላኔ በአደጋው የ253 ሰዎች ሕይወት ማለፉን ለደቡብ አፍሪካ ኢኤንሲኤ መገናኛ ብዙኃን ተናግረዋል።

ሮይተርስ የዜና ወኪል የግዛቱ ባለሥልጣናት ጠቅሶ የሟቾቹ ቁጥር 259 መድረሱን ዘግቧል።

አደጋው የተከሰተው በባህር ዳርቻዋ ክዋዙሉ ግዛት ውስጥ ሲሆን አሁንም በርካታ ሰዎች የደረሱበት አልታወቀም። የአደጋ ጊዜ ሰራተኞችም በሕይወት የተረፉ ሰዎችን እያፈላለጉ ነው።

ጎርፉ ባስከተለው የመሬት መንሸራተትም የከተማዋ ዋና ዋና መንገዶች የተዘጉ ሲሆን በርካታ ቤቶችም ወድመዋል።

የአየር ንብረት ለውጥ በደቡብ አፍሪካ ከወትሮው በተለየ ከባድ ዝናብ እንደሚያስከትል ተመራማሪዎች ሲያስጠነቅቁ ነበር።

በግዛቱ የጣለውን ከፍተኛ ዝናብ ተከትሎ በተከሰተ ጎርፍ ሥራ የሚበዛበት ወደብም ላልተወሰነ ጊዜ መዘጋቱ ተገልጿል።

በተከታታይ ለሦስት ቀናት በጣለው ዝናብ ሳቢያ የተከሰተው ጎርፍ የግዛቱን መንገዶች ፣ ድልድዮች እና ቤቶችን አውድሟል።

ትራንስኔት የተሰኘው የመንግሥት የሎጂስቲክስ ድርጅት በአካባቢው የጎርፍ አደጋው ባደረሰው ጉዳት ምክንያት የደርባን ወደብ ሥራ መጀመሩ እስከሚገለጽ ድረስ ላልተወሰነ ጊዜ ተዘግቷል ብሏል።

ወደ እቃ መጫኛ ሥፍራዎች [ተርሚናሎች] የሚወስዱት መንገዶችም በጎርፉ ምክንያት ክፉኛ የተጎዱ ሲሆን ወደ ውስጥ ለመግባትም አይቻልም።

በተጨናነቀው ፈጣን መንገድ አቅራቢያ የሚገኝ የእቃ ማጓጓዣ ኮንቴኔር መጋዘንም በጎርፍ ተጥለቅልቋል። በመቶዎች የሚቆጠሩ ኮንቴኔሮችም በጎርፍ ተወስደዋል።

ደርባን ከተማ በፍጥነት ወደ ሰብዓዊ ቀውስ እየተሸጋገረ ያለው የተፈጥሮ አደጋ ዋና ማዕከል ሆናለች።

ደርባንን የኢኮኖሚ እምብርት ወደ ሆነችው ጉዋቴንግ የሚያገናኘው ኤን3 ፈጣን መንገድም ተዘግቷል።

የኮሚዩኒኬሽን አገልግሎትም ተቋርጧል።

ሁለት ትላልቅ የቴሌኮም ኩባንያዎች ከ900 በላይ የሚሆኑ የሞባይል ስልክ ማማዎች እንደወደቁባቸው አስታውቀዋል።

የአገሪቱ ፕሬዚደንት ሲሪል ራማፎሳም የጉዳት መጠኑን ለማየት ወደ ሞዛምቢክ ሊያደርጉትን የነበረውን ጉዞ አቋርጠው በአደጋው ክፉኛ የተመታውን ኩዋዙሉ-ናታል ግዛት የባህር ዳርቻን ጎብኝተዋል።

ፕሬዚደንቱ የመንግሥት እና የሲቪል ማኅበራትን ምላሽን በመገምገም በአደጋው ለተጎዱ ማኅበረሰቦች ድጋፍ እንደሚደረግ ጽህፈት ቤታቸው አስታውቋል።