ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በተከሰከሰው የቻይና አውሮፕላን ውስጥ የነበሩ 132ቱም ሰዎች መሞታቸው ተገለጸ
ባሳለፍነው ሳምንት ሰኞ 132 ተጓዦችን እና የበረራ ሠራተኞችን አሳፍሮ ሲጓዝ የነበረው የቻይናው አውሮፕላን መከስከሱን ተከትሎ ሁሉም በውስጡ የነበሩት ሰዎች መሞታቸውን የቻይና ባለሥልጣናት አረጋገጡ።
ንብረትነቱ የቻይና ኢስተርን አየር መንገድ የሆነው አውሮፕላን በደቡባዊ ቻይና ኩንሚንግ ከተባለች ከተማ ወደ ጉዋንግዡ በመጓዝ ላይ ሳለ ነበር በድንገት ወደ ምድር ተምዘግዝጎ የተከሰከሰው።
በአካበቢው ሌት ተቀን ሲሰሩ የነበሩ የነፍስ አድን ሠራተኞች እስካሁን የ120 ሰዎችን አስክሬን ማንነት በዘረ መል ምርመራ አማካይነት መለየታቸውን ያስታወቁ ሲሆን የአውሮፕላኑን ሁለተኛ የበረራ መረጃ መመዝገቢያ ጥቁር ሳጥንን (ብላክ ቦክስ) በመፈለግ ላይም ናቸው።
ይህ ጥቁር ሳጥን አውሮፕላኑ እንዴት ሲበር እንደነበረ፣ ምን ዓይነት እክል እንዳጋጠመውና ለምን እንደተከሰከሰ ወሳኝ መረጃዎችን የያዘ ነው።
የመጀመሪያው ጥቁር ሳጥን ባለፈው ረቡዕ የተገኘ ሲሆን የዘርፉ ባለሙያዎች እንዲመረምሩት ወደ ቤይጂንግ ተልኳል። ይሄኛው ሳጥን በርካታ የድምጽ ቅጂዎችን እንደያዘ ይታመናል።
ምንም እንኳን በሕይወት የተረፉ ሰዎችን ማግኘት የሚለው ተስፋ አሁን ላይ የማይሆነ ነገር ቢሆንም በርካታ ቤተሰቦች የፍለጋ ቡድኑ ጥቅጥቅ ያለውን ደን መርምሮ እስኪጨርስና ዜናውን ይፋ እስከሚያደርግ ድረስ ለቀናት በተስፋ እየተጠባበቁ ይገኛሉ።
ነገር ግን ዉዡ በምትባለው ከተማ አቅራቢያ የሚገኘው ጉብታ ላይ ከፍተኛ ጭቃ መኖሩን ተከትሎ የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች ሥራቸውን በአግባቡ እንዳያከናውኑ እንቅፋት ሆኖባቸዋል።
የቻይና ሲቪል ኤቪዬሽን አስተዳደር ምክትል ዳይሬክተር የሆኑት ሁ ዤንጃንግ የሁሉንም ሟቾች አስክሬን እስከሚያገኙና የአደጋው መንስኤ እስኪታወቅ የፍለጋ ሥራቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ማስታወቃቸውን የቻይናው ሲና ድረ ገጽ ዘግቧል።
አደጋው የደረሰበት 737-800 ጄት አምራች የሆነው የአሜሪካው ቦይንግ ኩባንያ በበኩሉ የቴክኒክ ሠራተኞቹ የቻይና ሲቪል ኤቪዬሽን አስተዳደርና የአሜሪካ ብሔራዊ ትራንስፖርት ደኅንነት ቦርድ ለሚያደርጉት ምርመራ ድጋፍ እንደሚሰጡ አስታውቋል።
ባሳለፍነው ሳምንት የተከሰተውን ይህንን አደጋ ተከትሎ የቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ዢፒንግ ሁሉን አቀፍ ምርመራ እንዲካሄድ ማዘዛቸው ይታወሳል።
ከአስርት ዓመታት በኋላ መሰል የአውሮፕላን አደጋ ሲከሰትና በርካቶች ሲሞቱ በቻይና የመጀመሪያው ሲሆን በመላው አገሪቱም ከባድ ድንጋጤና ሐዘንን አስከትሏል።