ነፍሰጡር ፍቅረኛውን ገንዘብ ከፍሎ በአስቃቂ ሁኔታ ያስገደለው ግለሰብ ጥፋተኛ ተባለ

የፎቶው ባለመብት, @KEBA99
ከሁለት ዓመት በፊት ደቡብ አፍሪካ ውስጥ የተጸመውን አሰቃቂ የነፍሰጡር ሴት ግድያን የሟች ፍቅረኛ በማቀናበር ጥፋተኛ ነው ሲል የአገሪቱ ፍርድ ቤት ብይን ሰጠ።
ግድያው ከተፈጸመ በኋላ በደቡብ አፍሪካ ቁጣን ቀስቅሶ መነጋገሪያ የነበረው ትሼጎፋትሶ ፑሌ የተባለችው ነፈሰጡር እንድትገደል ፍቅረኛዋ ዋነኛው ተዋናይ መሆኑ ተገልጿል።
የጆሃንስበርግ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ንቱቱኮ ንቶኮዞ ሾባ የተባለው ግለሰብ ፍቅረኛው እንድትገደል በማቀድ እና ለገዳዩ ክፍያ በመፈጸም በወንጀሉ ውስጥ ባለው ተሳትፎ ጥፋተኛ አድርጎታል።
የ28 ዓመቷ ነፍሰጡር ደረቷ ላይ በጥይት ከተመታች በኋላ አስከሬኗ ዛፍ ላይ ተንጠልጥሎ የተገኘው ከሁለት ዓመት በፊት ነበር።
ግድያው ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳን ጨምሮ በአገሪቱ ሕዝብ ከፍተኛ ውግዘት ገጥሞት ነበር። ፕሬዝዳንቱ ደቡብ አፍሪካ "በዓለም ላይ ለሴቶች ደኅንነት የማታመች አገር ሆናለች" ሲሉ ተደምጠው ነበር።
በሴቶች ላይ የሚፈጸም የግድያ ወንጀልን ጨምሮ በዓለም ላይ በሴቶች ላይ ከፍተኛ ጥቃት ይፈጸምባታል በምትባለው ደቡብ አፍሪካ የፑሌ ሞት ብዙዎችን አስደንግጧል።
ፑሌን በመግደሉ የ20 ዓመት እስራት ተፈርዶበት የሚገኘው ሙዚካይሴ ማሌፋኔን በወንጀሉ ተሳትፎ አለው ስለተባለው ፍቅረኛዋ ምስክር ሆኖ የቀረበ ሲሆን ፍቅረኛዋ የግድያው ዋነኛ አቀናባሪ ነው ሲልም ተናግሯል።
ሾባ ሕጋዊ ሚስቱ ስለ እርግዝናው እንዳትያውቅ ፑሌን ለማስገደል እንደፈለገ ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል።
ግለሰቡ ነፈሰጡሯን ለማስገደል የወሰነው ከሚስቱን ላለመለያየት እና በወቅቱ ያገኘችውን የማኅበራዊ ዋስትና ክፍያ ለመካፈል አልሞ ነው ተብሏል። ተከሳሹ ወንጀሉን አልፈጸምኩም ብሎ ተከራክሯል።
ሆኖም የችሎቱ ዳኛ የቀረቡ ማስረጃዎች በሙሉ ግለሰቡ ጥፋተኛ እንደሆነ የሚያሳዩ ናቸው በማለት፣ የጥፋተኝነት ብይን አስተላልፈዋል። የቅጣት ውሳኔውም ከወራት በኋላ የሚሰጥ ይሆናል።
ከፍርድ ቤት አቅራቢያ የሞች ቤተሰቦች "ፍትህ አግኝተናል" እያሉ ደስታቸው በእንባና በመተቃቀፍ ሲገልጹ ተይተዋል። ፑሌ ስትገደል የመጀመሪያ ልጇን አርግዛ የነበረ ሲሆን ግድያው ከፍተኛ የትዊተር ዘመቻን ቀስቅሶ ነበር።
በዚህም ሳቢያ ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ ጾታታዊ ጥቃትን የሚያወግዝ መግለጫ አውጥተዋል። የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ለሴቶች የበለጠ አደገኛ ሆኗል ምክንያቱም "ጨካኝ ወንዶች ሴቶችን እና ሕፃናትን ለማጥቃት የእንቅስቃሴ ገደቦቹ ሽፋን ሆኗችዋል" ብለዋል።
በደቡብ አፍሪካ 51 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች ተጣማሪያቸው በሆኑ ሰዎች ጥቃት እንደደረሰባቸው የፕሬዚዳንቱ መግለጫ አመላክቷል።















