ደቡብ አፍሪካ ፡ ነፍሰ ጡር ፍቅረኛው እንድትገደል ያደረገው ግለሰብ ተፈረደበት

ንቱቱኮ ንቶኮዞ ሾቦ

የፎቶው ባለመብት, TWITTER/ @NPA_PROSECUTES

ታትሟል

በደቡብ አፍሪካ ነፍሰ ጡር ፍቅረኛው እንድትገደል ቅጥር ነፍሰ ገዳይ የገዛው ግለሰብ ዛሬ በጆሃንስበርግ ከተማ ተፈረደበት።

ባለፈው ሳምንት ነፍሰጡሯን የገደለው ግለሰብ 20 ዓመት እስር እንደተፈረደበት ይታወሳል።

የነፍሰጡሯ ሞት የአገሪቱን ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳን ጨምሮ በበርካታ ደቡብ አፍሪካውያን ዘንድ ከፍተኛ ቁጣን ቀስቅሶ ነበር።

ንቱቱኮ ንቶኮዞ ሾቦ ነፍሰጡር እጮኛው ትሼጎፋትሶ ፑሌ እንድትገደል ቅጥር ነፍሰ ገዳይ በመግዛት ተከስሶ ነበር።

ሾባ ለጥፋተኝነቱ የቅጣት ማቅለያ እንዲያቀርብ አልተጠየቀም ተብሏል።

ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር የ28 ዓመቷ ትሼጎፋትሶ ፑሌ አስከሬን አንድ ዛፍ ላይ ተንጠልጥሎ ሲገኝ የተለያዩ ቦታዎች ላይ በስለት መወጋቷን የሚያሳዩ ምልክቶች አካሏ ላይ ነበሩ።

ቅጥር ነፍሰ ገዳዩ የ31 ዓመቱ ምዚካይሴ ማሌፋኔ በጆሃንስበርግ በሚገኝ ችሎት ቀርቦ ጥፋተኛ ሆኖ በመገኘቱ የ20 ዓመት አስር ተፈርዶበታል።

ወንጀሉን የፈፀመው የልጅቷ የቀድሞ ፍቅረኛ ከፍሎት መሆኑን የተናገረው ማሌፋኔ በአሁኑ ጊዜ ግለሰቡ በእስር ቤት ይገኛል ሲል ፖሊሰ ተናግሯል።

ገዳይ በጠበቃው አማካኝነት ለፍርድ ቤቱ ባቀረበው የክስ ማቅለያ ላይ፣ 7,000 ራንድ [የደቡብ አፍሪካ ገንዘብ] በሟች የቀድሞ ፍቅረኛ ሊከፈለው ቢጠየቅም መጀመሪያ እምቢ ማለቱን ገልጿል።

ነገር ግን ክፍያው ወደ 70,000 ራንድ ከፍ ማለቱን እና መቀበሉን አስረድቷል።

ወ/ት ትሼጎፋትሶ ፑሌ አስከሬኗ ከመገኘቱ በፊት ለአራት ቀናት ጠፍታ ነበር

የፎቶው ባለመብት, @KEBA99

ማሌፋኔ ለፍርድ ቤቱ ሾባ "ባለቤቱ ስለተረገዘው ልጅ እንድታውቅ አይፈልግም ነበር" ሲል አስረድቶ ነበር።

ዐቃቤ ሕግ ባለፈው ሳምንት በቁጥጥር ስር የዋለውን ሾባን በነፍስ ግድያ ወንጀል፣ ለግድያ በማሴር እና ከፍትህ ለማምለጥ በመሞከር ክስ መስርቶበታል።

ትሼጎፋትሶ ፑሌ በተገደለችበት ወቅት የስምንት ወር ነፍሰ ጡር ነበረች።

የፑሌ አጎት የሆኑት ቱሚሳንግ ካታኬ፣ ሾባን በችሎት ፊት ቀርቦ ሲያዩት "የቆየው ቁስሌ ጠገግ ማለት ጀመረ" ብለዋል።

አጎትየው ሾባ ከፑሌ ጋር ይወጡ ይገቡ እንደነበር ገልፀው ቅርርባቸው "ምን ዓይነት እንደነበር" እንደማያውቁ ተናግረዋል።

እንደቤተሰቧ ከሆነ ሾባ ላልተለወደው ልጅ የሚያስፈልጉ ነገሮችን ለመገዛዛት ወደ ቤቱ እንድትመጣ ከጋበዛት በኋላ ፑሌ ወደ ቤቱ ሄዳ ነበር።

ከዚህ በኋላ ባለመግባባታቸው ታክሲ ጠርቶ እንደሸኛት ታውቋል።

በኋላ ፖሊስ ባደረገው ምርመራ የታክሲ ሹፌሯ የገደላት ግለሰብ ማሌፌኔ ሆኖ ተገኝቷል።

አስከሬኗ በዛፍ ላይ ተሰቅሎ በጆሃንስበርግ የምንዱባን ሰፈር ነዋሪዎች ከአራት ቀን ፍለጋ በኋላ የተገኘ ሲሆን ሁለት ቦታዎች ላይ በስለት መወጋቷም ይታይ ነበር።

ፖሊስ በግድያው ጠርጥረነዋል ያሉትን የ32 ዓመት ወጣት በቁጥጥር ስር ማዋላቸውን ወዲያው ይፋ ያደረጉ ቢሆንም ስሙን ግን ከመግለጽ ተቆጥበው ነበር።

በደቡብ አፍሪካ ባለፈው ሰኔ ወር ላይ በትሼጎፋትሶ ፑሌ ግድያ የተነሳ ከፍተኛ ተቃውሞ የተቀሰቀሰ ሲሆን በትዊተር ላይም #JusticeForTshego ዘመቻ ተጀምሯል።

የ31 ዓመቱ ምዚካይሴ ማሌፋኔ ወንጀሉን የፈፀምኩት የቀድሞ ፍቅረኛዋ ከፍሎኝ ነው ሲል ተናግሯል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳም ከዚያ በኋላ ባደረጉት ንግግር የጾታዊ ጥቃትን አውግዘው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ የሴቶችን ሕይወት ፈተና ውስጥ ጥሎታል በማለት "ነውጠኛ ወንዶች ይህንን የተቀመጠ ገደብ እየተጠቀሙ ሴቶችን እና ሕጻናትን እያጠቁ ነው" ሲሉ ተደምጠዋል።

በደቡብ አፍሪካ 51 በመቶ ሴቶች በሚቀርቧቸው ወንዶች የተነሳ የተለያዩ ጾታዊ ጥቃቶች ያጋጥማቸዋል።

ፕሬዝዳንት ራማፎሳ በአገሪቱ ከተካሄዱ በርካታ ፀረ ጾታዊ እንቅስቃሴዎች በኋላ አገራቸው "በዓለማችን ላይ ለሴቶች ምቹ ያልሆነች አገር" ሲሉ ተናግረዋል።