እስራኤል ውስጥ በስለትና በተሽከርካሪ በተፈጸመ ጥቃት አራት ሰዎች ተገደሉ

ታትሟል

በእስራኤል ደቡባዊ ክፍል በስለት በተፈጸመ ጥቃት አራት እስራኤላውያን መገደላቸውን እና በርካታ ሰዎች መቁሰላቸውን ፖሊስ አስታወቀ።

በእስራኤሏ ቤርሳቤህ ከተማ በሚገኝ የገበያ ማዕከል ውስጥ በተፈጸመው ጥቃት ሦስቱ ሰዎች በስለት ተወግተው ሲገደሉ አራተኛው በጥቃት አድራሹ በመኪና ከተገጨ በኋላ ሕይወቱ አልፏል።

ጥቃቱን ያደረሰው ግለለሰብ በአንድ የአውቶብስ አሽከርካሪ በጥይት ተምትቶ ተገድሏል።

የእስራኤል የአገር ውስጥ ደኅንነት ተቋም ጥቃቱን የፈጸመው ግለሰብ ከዚህ ቀደም እስላማዊውን ታጣቂ ቡድን አይ ኤስን በመደገፍ ታስሮ የነበረ እስራኤላዊ አረብ ነው ብሏል።

መሐመድ ጋሌብ አህመድ አቡ አልቂያን የተባለው ጥቃት አድራሹ ግለሰብ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህር እንደነበርም ተገልጿል።

አልቂያን እንደ አውሮፓውያኑ በ2015 ወደ ሶሪያ ተጉዞ አይኤስን ለመቀላቀል ሲያቅድ ተይዞ ጥፋተኛ ተብሎ ለእስር የተዳረገ ሲሆን እአአ 2019 ላይ ከእስር ተለቋል።

ፖሊስ እንዳለው አልቂያን ጥቃቱን የጀመረው አንዲት ሴትን በነዳጅ ማደያ ቦታ ላይ በስለት በመውጋት ነበር።

ከዚያም ወደ የገበያ ማዕከል መኪና በማሽከርከር አንድ ብስክሌተኛን ሆነ ብሎ በመግጨት ጥቃቱን ቀጥሏል።

አልቂያን ወደ ሌላ የገበያ ማዕከል በማቅናትም በአውቶብስ ሹፌሩ እስከተገደለበት ሰዓት ድረስ ብዙ ሰዎችን በስለት ወግቶ ጥቃት ማድረሱን ፖሊስ አብራርተዋል።

ጥቃት አድራሹ ትልቅ ቢላዋ ይዞ የሚያሳይ ምስል ተሰራጭቷል።

በጥቃቱ በርካታ ሰዎች የቆሰሉ ሲሆን የአንዳንዶቹ ጉዳት ከባድ በመሆኑ ወደ ሆስፒታል ተወስደዋል።

በእስራኤል መሰል ጥቃቶች የተለመዱ ቢሆንም፤ ይህ ግን ከዓመታት ወዲህ በርካታ ሰዎች የተጎዱበት አስከፊ ጥቃት ነው ተብሏል።

የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ናታሊ ቤኔት ክስተቱን "አስከፊ የሽብር ጥቃት" ያሉት ሲሆን ጥቃት አድራሹ ላይ የተወሰደውን እርምጃ "በብልሃት እና በጀግንነት" የተከናወነ ነው በማለት ተጨማሪ የሰው ህይወት እንዳይጠፋ አድርጓል ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ መንግሥታቸው በአሸባሪዎች ላይ ጠንካራ እርምጃ እንደሚወስድ እና ጥቃት አድራሾችን የሚደግፉትን ተከታትሎ እንደሚይዝ ተናግረዋል።