በአሜሪካ የ13 ዓመት ልጅ ሲያሸከረክረው የነበረው መኪና ተጋጭቶ 9 ሰዎች ሞቱ

ታትሟል

ባለፈው ማክሰኞች መጋቢት 06/2014 ዓ.ም. በአሜሪካዋ ቴክሳስ ግዛት የ13 ዓመት ልጅ ሲያሸከረክረው የነበረው መኪና ተጋጭቶ 9 ሰዎች መሞታቸውን ፖሊስ አስታወቀ።

ሐሙስ የአደጋውን መንስዔ ምርመራ እያካሄዱ የሚገኙ የፌደራል መንግሥቱ መርማሪዎች በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ታዳጊው ሲሸከረክረው የነበረው መኪና የፊት ግራ ጎማ ከፈንዳ በኋላ ከፊት ለፊቱ እየመጣ ከነበረ መኪና ጋር ተጋጭቷል ብለዋል።

በዚህ አደጋ ታደጊው አሸከርካሪው እና አብሮት የነረው ሰው እንዲሁም ታዳጊው ሲያሸከረክረው ከነበረ መኪና ጋር የተጋጨ ሽፍን (ቫን) መኪና ውስጥ የነበሩ 7 ሰዎች መሞታቸውን ፖሊስ አስታውቋል።

ከአጋው በሕይወት የተረፉ ሁለት የካናዳ ዜጎች የሕክምና ክትትል እያደረጉ ይገኛሉ።

የቴክሳስ የሕዝብ ደህኅንነት መሥሪያ ቤት ኃላፊ በግዛቲቱ የ13 ዓመት ልጅ መኪና እንዲያሸከረክር ሕጉ አይፈቅድም ብለዋል። በቴክሳስ ግዛት መኪና ማሸከርከር የሚችለው ትንሹ እድሜ 15 ሲሆን ይህም ፍቃድ ያለው አሰልጣኝ ወይም አዋቂ ከአሸከካሪው ጎን መሆን አለበት።

የብሔራዊ ትራንስፖርት ደኅንነት ቦርድ ኃላፊዎች በትናንቱ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የተጋጩት መኪናዎች በምን ያክል ፍጥነት እየተጓዙ እንደነበረ ግልጽ አይደለም ብለዋል።

ሁለቱ መኪኖች ከተጋጩ በኋላ በእሳት መያያዛቸውም ተገልጿል። የአደጋውን ሙሉ መንስዔ ለማወቅ ወራትን ሊወስድ ይችላል ብለዋል መርማሪዎቹ።

የቦርዱ አባላት በሸፍን መኪና ውስጥ የነበሩት አብዛኛዎቹ ተሳፋሪዎች የደኅንነት ቀበቶ አድርገው አልነበረም ብለዋል። ከተሳፋሪዎቹ መካከል አንድ ሰው በግጭቱ ኃይል ከመኪናው ተወርውሮ መውጣቱም ተገልጿል።

በሸፍኑ መኪና ውስጥ የነበሩት ሰዎች በኒው ሜክሲኮ ግዛት የሚገኝ የሳውዝዌስት ዩኒቨርሲቲ የጎልፍ ስፖርት ተወዳዳሪዎች እንደነበሩ ተገልጿል።