ለአብራሞቪች ፖርቹጋላዊ ዜግነት ሰጥተዋል የተባሉት ራባይ ምርመራ እየተደረገባቸው ነው

ሮማን አብራቮሚች

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል

ሩሲያዊው ቢሊዬነር ሮማን አብራሞቪች የፖርቹጋል ዜግነት እንዲኖራቸው አግዘዋል የተባሉት የአይሁድ እምነት አባት [ራባይ] ከፖርቹጋል እንዳይወጡ ታዘዙ።

የፖርቹጋል ባለሥልጣናት ሰውዬው በፖሊስ ተፈልገው ሲጠሩ በፍጥነት እንዲመጡም አዘዋቸዋል።

በርካታ አይሁዳዊያን እንዴት ፖርቹጋላዊ እንደሆኑ ለማወቅ ምርመራ እየተካሄደ ነው።

ባለፈው አርብ ሩሲያዊው ባለጠጋ ሮማን አብራሞቪች የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት ሃብት ንብረታቸው እንዳይንቀሳቀስ ማዕቀብ ጥሎባቸዋል።

የ55 ዓመቱ አብራሞቪች የቼልሲ እግር ኳስ ባለቤት ሲሆኑ ሃብት ንብረታቸው እንዳይንቀሳቀስ እንዲሁም ጉዞ እንዳያደርጉ ከታገዱ ሰባት ሩሲያዊያን ባለጠጋዎች አንዱ ናቸው።

የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ አብራሞቪችን ከቼልሲ ባለቤትን ማሕደር አንስቷል።

ሮማን አብራሞቪች ፖርቹጋላዊ ዜግነት የተሰጣቸው ባለፈው ዓመት በፈረንጆቹ ሚያዚያ 2021 ነበር።

የፑቲን ቀኝ እጅ ናቸው የሚባሉት ሮማን ይህን የዜግነት ወረቀት ያገኙት የአይሁድ ዘር ስላለባቸው ነው።

ብዙ ጊዜ የፖርቹጋላዊ ዜግነት ሂደት የሚከወነው ሊዝበን አሊያም ፖርቶ ውስጥ በሚገኝ አይሁዳዊያን መንደር ውስጥ ነው።

ራባይ ሊትቫክ በምሥራቃዊ ፓርቹጋል፤ ፖርቶ ውስጥ የሮማን አብራሞቪችን የዜግነት ወረቀት ሲያሳልጡ የነበሩ ግለሰብ ናቸው።

ራባይ ሊትቫክ ወደ ፖርቹጋል ሊሄዱ ሲዘጋጁ ነው በፓርቹጋል የደኅንነት ሰዎች ቁጥጥር ሥር የዋሉት። ፓስፖርትና የጉዞ ሰነዳቸውን የተነጠቁት ራባይ አስፈላጊ በሆነ ጊዜ ቀርበው መረጃ እንዲሰጡ ታዝዘዋል።

የፓርቹጋል ጁዲሺያል ፖሊስ አርብ ዕለት በሰጠው መግለጫ በዚህ የዜግነት አሰጣጥ ዙሪያ ሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር፣ ሙስና፣ ሰነድ ማጭበርበር አስተውያለሁ ብሏል።

የፖርቶ አይሁዳዊያን ማኅበር ምንም ሕገ ወጥ ነገር አላደረግንም፤ ስማችንን ለማጥፋት የተከፈተ ዘመቻ ነው ብሏል።