ተስፋ የተጣለባት የ20 ዓመቷ ኢትዮ-ጀርመናዊ ተዋናይት

የፎቶው ባለመብት, SARON
ሳሮን ደግነህ እባላለሁ።
20 ዓመቴ ነው።
የምኖረው ጀርመን፣ በርሊን ነው።
እናቴ ጀርመናዊት ስትሆን አባቴ ደግሞ ኢትዮጵያዊ ነው።
አንድ እህት አለችኝ።
ትወና የምወደው ሙያ ሲሆን ሥነ ልቦና ደግሞ እያጠናሁ እገኛለሁ።
በተለያዩ ፊልሞች ላይ የመሥራት ዕድል ገጥሞኛል።
በቴአትሮች ላይ መተወን ችያለሁ። የተለያዩ ማስታወቂያዎችን ለመሥራትም በቅቻለሁ። ጣሊያን እና ካናዳ ድረስ ተጉዤ ሠርቻለሁ።
ትወና ከልጅነቴ ጀምሮ እወድ ስለነበር አሁን እንደ ሙያ በመሥራቴ በጣም ደስተኛ ነኝ።
በነገራችን ላይ በልጅነቴ ጊታር እጫወት ነበር። ማርሻል አርትም ተምሬያለሁ።
ከልጅነቴ ጀምሮ ከወላጆቼ ጋር ወደ ብዙ አገራት ተጉዣለሁ። ከጀርመን እና ከኢትዮጵያ በተጨማሪ ከ20 በላይ አገሮችን ለማየት ችያለሁ።
"ተዋናይት መሆን አለብኝ ብዬ የወሰንኩት የመጀመሪያ ፊልሜ ላይ ስሠራ ይመስለኛል"
ወደ ትወና የገባሁት ሙያው በጣም ስለሚያስደስተኝ ነው።
በሙያዬ አዳዲስ እና የተለያዩ ገጸ ባህሪያትን መጫወት እና የተለያዩ ታሪኮችን መናገር እወዳለሁ።
እውነት ለመናገር የትርፍ ጊዜ ፍላጎቴን [ፈረንጆቹ ሆቢ የሚሉትን ለማለት ነው] ወደ ሙያ መለወጥ በመቻሌ የበለጠ ደስተኛ ነኝ።
ተዋናይት መሆን አለብኝ ብዬ የወሰንኩት የመጀመሪያ ፊልሜ ላይ ስሠራ ይመስለኛል። በጣም አስደሳች ከመሆን ባለፈ የሙያ መንገዴን የከፈተልኝም አጋጣሚ ነበር።
ለሙያው ያለኝን ፍቅር የተረዳሁት ለመጀመሪያ ጊዜ በቴአትር ቤት መድረክ ላይ ቆሜ በተመልካቾች ፊት ስጫወት ነበር።
የሚፈጠረው የአድሬናሊን ሆርሞን መነሳሳት [አድሬናሊን ሆርሞን የሰዎችን የደም ዝውውር፣ የአተነፋፈስ እና የሜታቦሊዝም መጠን በመጨመር ጡንቻዎች የሚያዘጋጅ ነው] እና ገጸ ባህሪውን ሙሉ በሙሉ ተላብሶ መጫወት በሚያስደንቅ ሁኔታ አስደሳች ነበር።
በጣም አስደሳቹ ነገር በተመልካቾች ላይ የማሳድረው ተጽዕኖ፣ ታሪኩን እንዴት በትኩረት እንደሚከታተሉት እና በውስጡም እንደሚዘፈቁ ማየት ነበር። ይህን ሁሉ ስመለከት እና ለሙያው ያለኝን ፍቅር ስረዳ ነው 'ይህንን ነው መሥራት የምፈልገው' ያልኩት።
ለትወና የሚረዳኝን ትምህርት ተከታትያለሁ።
ትምህርት ላይ እያለሁ በርሊን በሚገኝ የትወና ትምህርት ቤት በሳምንት የሦስት ሰዓት የትወና ሥልጠና እወስድ ነበር።
ትምህርቱ የተለያዩ የትወና ገጽታዎችን ይሸፍናል።
በርሊን በሚገኘው የዶቼ ቴአትር [የጀርመን ቴአትር] እተውን በነበረበት ወቅት ደግሞ በሳምንት 5 ጊዜ ለአራት ሰዓታት የሁለት ወር ሥልጠና ወስጃለሁ።
በነገራችን ላይ ከ9 እስከ 12ኛ ክፍል በምማርበት ወቅትም ባበልስበርግ ፊልም ትምህርት ቤት እማር ነበር።

የፎቶው ባለመብት, SARON
"ለዚህ ድራማ ሲባል አረብኛን በኢራቃዊያን ዘዬ መማር ነበረብኝ"
የመጀመሪያዬ የፕሮፌሽናል የትወና ጉዞዬ የሚጀምረው በቴአትር ነበር። በፈረንጆቹ 2014 ይመስለኛል።
ትዝ ይለኛል ወጣ ያለ ባህሪ ያላት ተማሪን ሆኜ ነበር የተጫወትኩት። ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ መድረክ ወጥቼ በተመልካቾች ፊት ለመጫወት በጣም ጓጉቼ ነበር።
ተማሪዋን ሙሉ ለሙሉ ተላብሼ የተጫወትኩ ሲሆን ስጫወታትም በጣም እየተዝናናሁ ነበር።
መጨረሻ ላይ የታዳሚው ጭብጨባ በእርግጥም ለሥራው ድምቀት ነበር።
በኋላም በአንዳንድ አጫጭር ፊልሞች ላይ ተሳትፌያለሁ።
በሌላ በኩል ለቲቪ ድራማ የመጀመሪያ ቀረጻዬን ያደረኩት በ2017 ነበር።
በወቅቱ የ14 ዓመት የኢራቅ ስደተኛን በመላበስ ነው የተጫወትኩት።
ለዚህ ድራማ ሲባል አረብኛን በኢራቃዊያን ዘዬ መማር ነበረብኝ። ይህ ደግሞ በጣም ፈታኝ አድርጎት ነበር።
በዚህ ጊዜ የተገነዘብኩት ነገር በተሰበሰቡ ሰዎች ፊት መጫወት የሚያስፈራ መሆኑን ነው።
ምክንያቱም እኔ ባላያቸውም በፊልም ቀረጻ ወቅት ከቴአትር ቤቱ በበለጠ ከካሜራው ጀርባ ያሉ ብዙ ሰዎች በቅርብ ሆነው የሚመለከቱኝ አሉ።
ያም ቢሆን በጣም አስደሳች ነበር። አንዴ ድንጋጤው ከጠፋ በኋላ ከካሜራ ፊት መሆን ያስደስተኝ ነበር።
ፊልም አሠራር ከቴአትር በጣም የተለየ ነው።
ሁለቱም ግን አስደሳች ናቸው።
ከቴአትር በበለጠ ፊልም ላይ ትክክለኛ ለመሆን እየጣሩ መሥራትን ስለሚጠይቅ የፊልም ሚናው ከቴአትር ይለያል።
በአጠቃላይ ወደ 10 የሚጠጉ ፊልሞች እና ሁለት ማስታወቂያዎች ላይ ተሳትፌያለሁ።
የተለያዩ ዘውጎችም ነው የተጫወትኩት- የወንጀል ፊልሞች፣ አጫጭር ፊልሞች እና የኮሜዲ ፊልሞች ላይ ተሳትፌያለሁ።
ለሱፐርማርኬት፣ ለንግድ ትርዒት እና ለአንድ ትልቅ የኢንሹራንስ ኩባንያ የፎቶ ሞዴል ሆኜም አስተዋውቄያለሁ።
"ፊልሙን ከሦስት ሚሊዮን በላይ ሰዎች ተመልክተውታል"
ዳስ ኤርስተ በተባለው የጀርመን ቴሌቪዥን ጣቢያ በተላለፈው 'ቢሊ ኩክኩክ አንጌሴልት' የተባለ የቴሌቪዝን ፊልም ተውኛለሁ። በአጭር ጊዜ ውስጥ ከሦስት ሚሊዮን በላይ ሰዎች ተመልክተውታል።
ፊልሙ በዝቅተኛ ኑሮ ደረጃ የሚገኙ እና ስደተኛ ወጣቶችን አሰባስቦ በሚያሠለጥን አንድ የቦክስ አሠልጣኝ ሕይወት ዙሪያ ያጠነጥናል።
በዚህ ፊልም በሁለተኛ መሪ ተዋናይነት ሳሚ የምትባል እናትና አባቷን ያጣች እና ጥሩ የቦክስ ችሎታ ያላት አንዲት የአፍጋንሲታን ስደተኛ ወጣትን ወክያለሁ።
ለፊልሙ በኤጀንሲዬ በኩል ነው ወደ ተዋናይት ምልመላ [ካስቲንግ] የተጋበዝኩት።
መልማዮችን እና ዳይሬክተሩን በትወናዬ እስከማሳምን ድረስ ሠርቻለሁ።
በፊልሙ ላይ ከአፍጋኒስታን የመጣች የ17 ዓመት ቦክሰኛን ሆኜ ተጫውቻለሁ።
ቦክስ የምትወድ ሲሆን በጣም ጠንካራ ልጅም ነች።
ከጀርመን ላለመባረር የነበራት አንድ የመጨረሻ ዕድል ከጀርመን ሻምፒዮኗ ጋር መወዳደር ነው።
ለፊልሙ ሲባል ተጨማሪ የቦክስ ስልጠናም አግኝቻለሁ። ይህም በጣም ጥሩ ልምድ ነበር።
እኔ እስከሚገባኝ ድረስ ፊልሙ በጣም ጥሩ ተቀባይነት አግኝቷል።
ጓደኞቼ እና ቤተሰቦቼ ወድደውታል።
አንዳንዶቹ በአስቂኝ ክፍሎቹ ተደስተዋል፤ ሌሎች ደግሞ የቦክስ ትዕይንቶቹን በጣም ወድደዋቸዋል። የፖለቲካ ጭብጡን የወደዱትም አሉ።
አንዳንዶች ደግሞ አጨራረሱ በጣም ስሜታዊ ሆኖ አግኝተውታል።
በጦማሮች ላይም አንዳንድ ጥሩ አስተያየቶችን አንብቤያለሁ።

የፎቶው ባለመብት, SARON
"ግማሽ ኢትዮጵያዊ መሆኔ የተለያዩ የዘር ሃረግ ያላቸውን ሰዎች ተላብሼ እንድጫወት ዕድል ሰጥቶኛል"
እስካሁን ካናዳ በሠራሁት አጭር ፊልም በባርሴሎና ፊልም ፌስቲቫል "ምርጥ ተዋናይት" ተብዬ ተሸልሜያለሁ።
በጣም ደስ የሚል አጋጣሚ ነበር።
የፊልሙ ርዕስ ስቱፒድ ስማርትፎን (Stupid Smartphone) ይባላል።
ጭብጡ ከቤተሰባችን ጋር ሳይሆን በስልኮቻችን ላይ የምናጠፋው ጊዜ መጠን የሚመለከት ነው።
እውነት ለመናገር ዘርፉ ከፍተኛ ውድድር ስላለው ራሴን ለመጠበቅ እና የቻልኩትን ያህል ለማድረግ እሞክራለሁ።
ግማሽ ኢትዮጵያዊ መሆኔ የተለያዩ የዘር ሃረግ ያላቸውን ሰዎች ተላብሼ እንድጫወት ዕድል ሰጥቶኛል። ይህም ከሌሎች የተሻለ የመጠቀም ዕድል ፈጥሮልኛል።
ከዚያ ውጭ ከሌሎች ጋር ራስን ማወዳደር ብዙም አስፈላጊ አይደለም።
ለተዋናይ ምልመላ ሄዶ አይመጥኑም ከተባሉ [ይህ ብዙ ጊዜ የሚከሰት ስለሆነ] በኋላ ሌላው ሰው አልፎ እንዴት እኔ አልተሳካልኝም? በማለት ተስፋ መቁረጥ አያስፈልግም።
ሙያው ጫና ያለበት በመሆኑ ጥሩ የሕይወት ሚዛን ያስፈልጋል። ከሥራው ውጭ እንደ ስፖርት ያሉ ሌሎች ነገሮችን ማሰብ በጣም አስፈላጊ ነው።
ጓደኞቼ እና ቤተሰቦቼ በመደገፍ፣ ግፊቱን በመቀነስ ያግዙኛል።
እንዳልወድቅ በማድረግም በራሴ ላይ ተጨማሪ ጫና ላለመፍጠር መሞከር አለብኝ።
በእርግጥ ይህ ሁል ጊዜ ቀላል አይደለም [ሳቅ]።
እንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ስገባ ቤተሰቦቼ ሁል ጊዜም ዝግጁ ናቸው።
ከሥራዬ የምወደው ነገር አዳዲስ ቦታዎችን እና ሰዎችን መተዋወቅ መቻሌ ነው።
ሌሎች ሊመለከቷቸው የሚወዷቸውን ታሪኮች መፍጠር እና ሌሎች ሰዎች እንዲለወጡ ምክንያት መሆንም ሌላው አስደሳች ነገር ነው።
ከምርጥ ገጠመኞቼ አንዱ ጣሊያን ተጋባዥ ተዋናይ የሆንኩበት ነው ማለት እችላለሁ።
በጀርመን ቴአትር [ዶቼ ቴአትር] በነበርኩበት ወቅት ወደ ጣሊያን በመጓዝ አንድ ፌስቲቫል ላይ ዝግጅታችንን እንድናቀርብ ዕድል አግኝተናል።
የጣሊያን ታዳሚዎች በጣም ጓጉተው ከመጠበቃቸውም በላይ ለእኛ በጣም ጥሩ አጋጣሚ ነበር።
ከዘንባባ ዛፎች አጠገብ እና በጣሊያን መንፈስ መሥራት ልዩ ነገር ነው። በጀርመን ቋንቋ ስንጫወት የነበረ ቢሆንም በመድረኩ ላይ ቃለ ተውኔታችንን በጣሊያንኛ ለታዳሚው እየተተረጎመ ይታይ ነበር።

የፎቶው ባለመብት, SARON
"ሥነ ልቦና ከትወና ጋር ሊጣመር ይችላል"
ከትወና ውጭ ሥነ ልቦና እያጠናሁ ነው። ሕልሜ የሥነ ልቦና ባለሙያ መሆን ነው። በጣም ጥሩው ነገር ከትወና ጋር ሊጣመር መቻሉ ነው።
በጥሩ ጊዜ አስተዳደር (time management) የሥራ እና የትምህርት ጊዜዬን ሚዛን እጠብቃለሁ።
በግላዊው መንገድ ዳር እንዳልቀር ሁል ጊዜም ራሴን ነጻ ለማድረግ እሞክራለሁ። ምክንያቱም ሁለቱም ሙያዎች ለእኔ እኩል አስፈላጊ ናቸው።
ምንም እንኳን ሁልጊዜ ቀላል ባይሆንም የፊልም ሥራ ድንገተኛ የሚባል ዓይነት ነው።
በሳምንቱ መጨረሻ ላይ ባሉኝ ግላዊ ዕቅዶች ላይ ጣልቃ የሚገቡ ብዙ የሥራ ጥያቄዎችን አገኛለሁ።
እንደዚህ ዓይነት ነገር ሲያጋጥመኝም እንደሁኔታው ለመራመድ እሞክራለሁ።
እዚህ ላይ ዝግጁ ሆኖ መጠበቅ አስፈላጊ ነው ብዬ አስባለሁ።
በዚህ [የፈረንጆች] ዓመት የመጀመሪያ ዲግሪዬን በሳይኮሎጂ አገኛለሁ።
ቀጥሎ ደግሞ የማስተርስ ዲግሪዬ ይመጣል።
ትምህርቱ በንድፈ ሐሳብ የተሞላ እና ሳይንሳዊ ነው።
በጣም አስደሳች ቢሆንም ፈታኝ ጭምር ነው።
አብዛኛውን ጊዜዬን ከትምህርቴ ጋር በተያያዘ አሳልፋለሁ። ይህንንም እወደዋለሁ።
ትወና ደግሞ ትልቅ ሚዛን ይሰጠኛል።
የሥነ ልቦና ባለሙያ እና ተዋናይ ሆኜ መሥራት እፈልጋለሁ። ሁለቱንም መተው አልፈልግም።
እስካሁን ድረስ ሁለቱንም በመሥራት ጥሩ ውጤት እያስመዘገብኩ ነው።
ተዋናይ ለመሆን ስወስን ቤተሰቤ ድጋፍ አድርገውልኛል።
እናቴ በቴአትር ቤት መድረክ ላይ ስተውን ልታየኝ ሁሌም ትጓጓለች።
አባቴ አሁንም ከእኔ ጋር የተዋናይት ምልመላ የሚመስል ሥራ ያዘጋጅልኛል። በተጨማሪም ወጣቶችን በማውጣት የታወቀ ፕሮፌሽናል የተዋናይ ምልመላ ድርጅት እንዳገኝ ረድቶኛል።
ሁለቱም እየረዱኝ ሲሆን ትላቅ ድጋፍም ነው የሚሰጡኝ።
ባለፈው ዓመት በኢትዮጵያዊ ሥራ ላይ ለመጫወት ችያለሁ።
እንደ አለመታደል ሆኖ ፕሮጀክቱ በኮሮና ምክንያት ተቋርጧል።
ሆኖም በጣም ወድጄዋለሁ። ሌላ ሥራ ብሠራ ደስተኛ ነኝ።
ከአሥር ዓመታት በኋላ ሕልሜ በተለይም በዓለም አቀፍ ደረጃ ብዙ ፊልሞችን ለመሥራት ነው።
እንዲሁም በሥራዬ በመዝናናት ለመቀጠል እፈልጋለሁ።
ሕልምና እና ምኞታቸውን ለማሳካት በሚያደርጉት ሩጫ ሁሉም ሰዎች በፍጥነት ተስፋ እንዳይቆርጡ ማበረታታት እፈልጋለሁ።
እያንዳንዱ ውድቀት እና ፈተና የበለጠ የበሰለን እና ጠንካራ ያደርገናል [ሳቅ]።
በጣም አመሰግናለሁ!















