በሺዎች የሚቆጠሩ የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ መምህራን ደሞዝ ከተከፈላቸው ከዓመት በላይ እንዳለፋቸው ገለጹ

የፎቶው ባለመብት, YASUYOSHI CHIBA
ከ7ሺህ በላይ የመቀለ ዩኒቨርሲቲ መምህራን ደሞዝ ሳይቀበሉ አንድ ዓመት እንዳለፋቸው ለቢቢሲ ተናገሩ።
መምህራኑ ምንም እንኳ የፌደራል መንግሥቱ ቅጥረኛ ቢሆኑም "ደመወዝ ስላልተላከልን የከፋ ችግር ውስጥ እንገኛለን" ብለዋል።
ትምህርት ሚኒስቴር በበኩሉ ከትግራይ ክልል የወጡ መምህራንን ወደ ሌላ ተቋማት ማሸጋገሩን እና በክልሉ ላሉት ግን ምንም ማድረግ እንደማይችል ገልጿል።
በዩኒቨርሲቲው የህክምና ትምህርት ቤት ባልደረባ የሆኑት አንድ ሠራተኛው፤ የሚበሉት ሳይኖራቸው በባዶ ሆዳቸው ወደ ሥራ መጥተው ሕክምና እያደረጉ እራሳቸውን ስተው የሚወድቁ ሐኪሞች ስለመኖራቸው ያስረዳሉ።
በትግራይ ክልል ጦርነት ከተቀሰቀሰ በኋላ የመቀለ ዩኒቨርሲቲ 7ሺህ ሠራተኞች ደሞዝ እንዳልተከፈላቸው እና እጅግ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ ይህ የሕክምና ትምህርት ቤት ባልደረባ ይገልጻሉ።
"የፌደራል ተቋም ብንሆንም፤ የፌደራል መንግሥቱ በጀት ሳይልክልን ቀርቷል" በማለት ቅሬታቸውን ለቢቢሲ አቅርበዋል።
የትምህር ሚኒስቴር ሚኒሰትር ዲኤታ ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) በትግራይ ላሉ ሠራተኞች ምንም ማድረግ አንችልም ይላሉ።
"ከክልሉ ሸሽተው የወጡ የዩኒቨርሲቲ ባልደረቦች ወደ ሌሎች ከተሞች ተዘዋውረዋል፤ ተማሪዎችም እንዲሁ። ግን በአሁኑ ወቅት በክልሉ ላሉት ምንም ማድረግ አንችልም" ሲሉ ሚኒስትር ዲኤታው ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ዩኒቨርሲቲዎች ዓመታዊ በጀታቸውን የሚያገኙት ከፋይናንስ ሚኒስቴር መሆኑም አክለው ገልፀዋል።
ቢቢሲ ያነጋገረው ይህ የዩኒቨርሲቲ ባልደረባ ልጆቻቸው በምግብ እጥረት እየተጎዱ መሆኑን እና ሁኔታዎች እየተባባሱ በሄዱ ቁጥር ተስፋ መቁረጥ ውስጥ መግባታቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
"ስለ ሁኔታው ለልጆቻችን መግለጽ ከባድ ነው። ይህ መቼ እንደሚያቆም አናውቅም፤ ደመወዛችንን መቼ እንደምናገኝ፤ ክልካለው መቼ እንደሚቆም አናውቅም። የምንሸሽበት ቦታ እንኳ የለም።" በማለት ያሉበትን ሁኔታ ይገልጻሉ።
ያለውን ሁኔታ ለመቋቋም ልጆቻቸውን ወደ ገጠራማ የትግራይ አካባቢ የላኩ መምህራን መኖራቸውን የሚገልጹት እኚህ የአይደር ሕክምና ትምህርት ቤት ባልደረባ፤ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን እና የትግራይ ታጣቂ ኃይሎችን የተቀላቀሉም አሉ ይላሉ።
ከሁለት ወራት ገደማ በፊት የአይደር ሪፈራል ሆስፒታል ሠራተኞች በክልሉ ባለው መሠረታዊ የሕክምና ግብዓት እጥረት ምክንያት በትግራይ የሕክምና አገልግሎት ጥረት ደረጃ እየወረደ መሆኑን ረዘም ባለ ጽሑፋቸው አስረድተው ነበር።
በትግራይ ተቅስቅሶ ወደ አጎራባች ክልሎች የተዛመተው እና 16 ወራትን ያስቆጠረው የትግራይ ጦርነት ከፍተኛ የሆነ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ውድመትን አስከትሏል።












