ሩሲያ እና ዩክሬን: በጦርነት ግማሽ ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች ከዩክሬን መሸሻቸው ተነገረ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ዩክሬን ውስጥ እየተካሄደ ባለው ጦርነት ሳቢያ ግማሽ ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች ጦርነቱን ሽሽት ከቤታቸው መፈናቀላቸውን የተባበሩት መንግሥታት አስታወቀ።
አንድ የመንግሥት ባለሥልጣን እንዳሉት በአገሪቱ ሁለተኛ ትልቅ ከተማ ካርኪቭ ላይ በቀጠለው የከባድ መሳሪያ ጥቃት በርካታ ሰላማዊ ሰዎች ተገድለዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ መብት ጉዳዮች ከፍተኛ ባለሥልጣን የሆኑት ሚሼል ባሽሌት እንዳሉት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ከመሬት በታች ባሉ የባቡር ጣቢያዎች ውስጥ በሚገኙ ጊዜያዊ የቦምብ ጥቃት መጠለያዎች ውስጥ ተጨናንቀው ይገኛሉ።
ባለፈው ሐሙስ የሩሲያ ወረራ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ሰባት ህጻናትን ጨምሮ 102 ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውንና ከ300 በላይ ደግሞ መቁሰላቸውን የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ጽህፈት ቤት ገልጿል።
"ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ትክክለኛው አሃዝ በጣም ከፍተኛ ሊሆን እንደሚችል ስጋት አለኝ" ብለዋል ባሽሌት።
ዋና ከተማ ኪዬቭን፣ ካርኪቭን እና ቼርኒሂቭን ጨምሮ መላዋ ዩክሬን በሩሲያ ኃይሎች ጥቃት ስር ስትሆን ጦርነቱ ተባብሶ እየተካሄደ ነው።
ዩክሬን በስተሰሜን ከቤላሩስ ጋር በምትዋሰንበት ድንበር አካባቢ የሩሲያ እና የዩክሬን ባለሥልጣናት ጦርነቱ ከጀመረ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ውይይት ጀምረዋል።
የዩናይትድ ኪንግደም የመከላከያ ሚኒስቴር አብዛኛው የሩሲያ ኃይል የሚገኘው ከዩክሬን ዋና ከተማ ኪዬቭ 30 ኪሎሜትሮች ወጣ ብሎ ነው ያለ ሲሆን ግስጋሴያቸውም በዩክሬናውያን ከባድ የመከላከል ውጊያ መገታቱንም አመልክቷል።
በኪየቭ በርካታ ስፍራዎች ላይ የጎዳና ላይ ውጊያ እየተካሄደ ቢሆንም ተጥሎ የነበረው የሰዓት እላፊ ተነስቶ ተደብቀው የነበሩ ነዋሪዎች የሚያስፈልጋቸውን ምግብና ሌሎች ነገሮችን ለመግዛት እየወጡ ነው።
በስተሰሜንና ሰሜን ምሥራቅ የሚገኙት ካርኪቭ እና ቼርኒሂቭ ከተሞችም ሌሊቱን በሙሉ በሩሲያ ከባድ መሳሪያዎች ሲደበደቡ ቢያድሩም አሁንም በዩክሬን ኃይሎች እጅ ስር መሆናቸው ተነግሯል።
የዩክሬን የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር አማካሪ በፌስቡክ ገጻቸው ላይ እንዳሉት "ካርኪቭ በከባድ ሮኬት ተደብድባለች። በርካቶች ሲገደሉ በመቶዎች የሚቆጠሩት ደግሞ ቆስለዋል።"
በደቡብ በኩል የሩሲያ ኃይሎች ከዓመታት በፊት በቁጥጥራቸው ስር ካስገቧት ክራይሚያ አቅራቢያ የምትገኘውን ስልታዊ ወደብ ማሪዮፖልን ለመቆጣጠር እየጣሩ ነው።
ቀደም ሲል በአውሮፓ ትልቁ የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ ማዕከል እንደሆነ የሚነገርለት ዛፖሪዢዢያ በሩሲያ ሠራዊት ቁጥጥር ገብቷል ተብሎ ቢዘገብም፣ ዩክሬን ግን ሐሰት ነው ስትል አስተባብላለች።












