ሩሲያ እና ዩክሬን: በዩክሬን ጦርነት ሳቢያ በደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንትና በውጭ ጉዳይ ሚኒስትራቸው መካከል አለመግባባት መፈጠሩ ተዘገበ

ፕሬዚደንት ፑቲንና ፕሬዚደንት ራማፎሳ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ደቡብ አፍሪካ እና ሩሲያ ጠንካራ የኢኮኖሚ ትስስር አላቸው።
ታትሟል

የሩሲያ ጦር በዩክሬን ላይ የከፈተውን ወረራ ተከትሎ በደቡብ አፍሪካው ፕሬዚደንት ሲሪል ራማፎሳ እና በውጭ ጉዳይ ሚኒስትራቸው ናሌዲ ፖንዶር መካከል ከፍተኛ ልዩነት መፈጠሩን የአገሪቱ የዜና አውታሮች ዘገቡ።

ኒውስ 24 እንደዘገበው ልዩነቱ የተፈጠረው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ ናሌዲ ፓንዶር መሥሪያ ቤት ሩሲያ ከዩክሬን በአስቸኳይ ለቅቃ እንድትወጣ የሚጠይቅ መግለጫ ካወጣ በኋላ ነው።

ይህም ፕሬዝደንት ሲሪል ራማፎሳን ክፉኛ አስቆጥቷል።

የዜና አውታሩ በስም ያልገለጻቸውን ውስጥ አዋቂ ምንጮችን ጠቅሶ እንደዘገበው ፕሬዚደንቱ ደቡብ አፍሪካ በጦርነት ወቅት ለአንድ አካል ወግና እንደማትቆም አፅንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።

ኒውስ 24 አክሎም ገዥው የደቡብ አፍሪካ ፓርቲ አፍሪካ ናሽናል ኮንግረስ (ኤኤንሲ) ዓለም አቀፍ ግንኙነት ንዑስ ኮሚቴ ሰኞ በሚያካሂደው ስብሰባ በሚኒስትር ፓንዶር ላይ ቅጣት ያስተላልፋል ተብሎ እንደሚጠብቅ ዘግቧል።

ሰንዴይ ታይምስ በበኩሉ ፕሬዚደንት ራማፎሳ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል የወጣው መግለጫ የደቡብ አፍሪካን አቋም የሚቃረን ነው በማለት በመግለጫው ደስተኛ እንዳልሆኑ ለፕሬዚደንቱ ቅርብ ናቸው ያላቸውን ምንጮች ጠቅሶ አስነብቧል።

"ፕሬዚደንቱ መግለጫው ከመውጣቱ በፊት አላዩትም። በጉዳዩ ላይም ተነጋግረው አልተስማሙበትም። በአገሪቷ ዓለም አቀፍ ግንኙነትና ኮርፖሬት ተቋማት ውስጥ ከሩሲያ ጋር ጠላት መሆን አለብን የሚል አጀንዳ ያላቸው ሰዎች አሉ" ሲሉ ስማቸው ያልተጠቀሱ ምንጭ ለሰንደይ ታይምስ ገልጸዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ ፓንዶር ቃል አቀባይ የሆኑት ሉንጋ ንጌንጌሌሌ በበኩላቸው ፕሬዚደንቱ መሥሪያ ቤቱ ባወጣው መግለጫ ደስተኛ አለመሆናቸውን እንደማያውቁ ተናግረዋል።

ጨምረውም የሩሲያ ጦር ከዩክሬን እንዲወጣ የተደረገው ጥሪ "የሰላም ድርድር እንዲካሄድ ዕድል ለመስጠት ነው" ሲሉ ለጋዜጣው ተናግረዋል።