በጀርመን በሰዓት 417 ኪሎ ሜትር ያሸከረከረው ግለሰብ ምርመራ ተከፈተበት

የፎቶው ባለመብት, AFP
ጀርመን በምቹ አውራ ጎዳናዎቿ አሸከርካሪዎች ያለ ፍጥነት ገደብ መኪኖቻቸውን እንዲያከንፉ ትፈቅዳለች።
የቼክ ሪፓብሊኩ ሚሊየነር ግን ቅንጡ መኪናውን በጀርመን ጎዳና ላይ 417 ኪሎ ሜትር አክንፏል መባሉ የጀርመን ባለሥልጣናትን አላስደሰተም።
ራዲም ፓሴር በቸልተኝነት በከፍተኛ ፍጥነት መኪና ማሸከርከር በሚል ምርመራ ተከፍቶበታል።
አሸከርካሪው ጥፋተኛ ሆኖ የሚገኝ ከሆነ የሁለት ዓመት እስር ወይም የገንዘብ መቀጮ ይጠብቀዋል ተብሏል።
ይህ የቼክ ሪፐብሊክ ባለጸጋ በቅንጡዋ ቡጋቲ ካይረን መኪናው ከጀርመኗ መዲና በርሊን ወደ ሃኖቨር በሚወስደው አውራ ጎዳና ላይ በከፍተኛ ፍጥነት ሲጓዝ የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል በዩቲዩብ ገጹ ላይ ከለጠፈ በኋላ ነው በጀርመን ባለሥልጣናት ዓይን ውስጥ የገባው።
በዚህ ቪዲዮ ላይ የመኪናዋ ፍጥነት መለኪያ መኪናዋ በሰዓት 417 ኪሎ ሜትር እየበረረች እንደሆነ አሳይቷል።
ራዲም ፓሴር በዩቲዩብ ገጹ ላይ ይህን ቪዲዮን ሲያጋራ ለደኅንነት ቅድሚያ መሰጠቱን በጽሁፍ አመልክቷል። ሚሊየነሩ የቼክ ዜጋ መኪናዋን በፍጥነት ያሸከረከረው የትራፊክ መጨናነቅ ባልነበረት እሁድ ጠዋት ላይ መሆኑ እንዲሁም መንገዱ በነበረው መልካም የአየር ጸባይ ጥርት ብሎ ይታየው እንደነበረ ገልጿል።
ይሁን እንጂ የግለሰቡ ተግባር የበርካቶችን ትኩረት ስቦ ጉዳዩ የጀርመን ፖሊስ ጋር ደርሷል። የትራንስፖርት ሚኒስትሩ ቮልከር ዊሲንግ የአሸካርካሪውን ተግባር ኮንነዋል።
ኤኤፍፒ የዜና ወኪል የትራንስፖርት ሚኒስትሩ ሁልጊዜም ተሸከርካሪዎች በቁጥጥር ሥር መሆን አለባቸው በማለት የአሸከርካሪውን ተግባር "በቸልተኝነት የተሞላ" ስለማለታቸው ዘግቧል።












