ኢንሳ ለዋልታ የፌስቡክ ገጽ መጠለፍ ከህወሓት ጋር ግንኙነት አላቸው ያላቸውን ሰዎች ተጠያቂ አደረገ

የዋልታ ሎጎ

የፎቶው ባለመብት, Walta TV

ታትሟል

የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል የፌስቡክ ገጽ መጠለፍ ከህወሓት ጋር ግንኙነት አላቸው ያላቸን ግለሰቦች ተጠያቂ አደረገ።

የኤጀንሲው ምክትል ኃላፊ አቶ ከፍያለው ተፈራ መረጃ መንታፊዎች የተቋሙን የፌስቡክ ገጹን ለመጥለፍ 'ራንሰምዌር' የተሰኘ ስልትን ተጠቅመዋል ብለዋል።

እስካሁን ድረስ የመረጃ መንታፊዎቹን ማንነት ለመለየት ምርመራ እተካሄደ ነው ያሉት ምክትል ኃላፊው፤ ክህወሓት ጋር ግነኙነተ ያላቸው ሰዎች ግን ተሳታፊ ስለመሆናቸው ጠቁመዋል።

ነገር ግን ኃላፊው ስለግለሰቦቹ ማንነት የሰጡት ዝርዝር የሌለ ሲሆን፣ ጉዳዩን በሚመለከትም ከህወሓት በኩል አስካሁን የተባለ ነገር የለም።

ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ግንኙነት ያለው ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል የፌስቡክ ገጽን መልሶ ለመቆጣጠር የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ ከሜታ (ፌስቡክ) ጋር እየተነጋገረ መሆኑን አቶ ከፍያለው ተፈራ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

መንታፊዎቹ ከሰኞ አመሻሽ ጀምሮ የፌስቡክ ገጹን በቁጥጥራቸው ሥራ ካዋሉ በኋላ የተለያዩ ይዘቶችን በገጹ ላይ ሲለጥፉ እና ሲሰርዙ የቆዩ ሲሆን የፌስቡክ ገጹ መልሶ እንዲለቀቅላቸው 5ሺህ ዶላር የአሜሪካን ዶላር ክፍያ መጠየቃቸውን አቶ ከፍያለው ይናገራሉ።

"ችግሩ የተፈጠረው ቀድሞውኑ እንደዚህ አይነት አካውንቶች ሲከፈቱ ታማኝ ናቸው ተብለው ኃላፊነት የተሰጣቸው ሰዎች ይህን ችግር ሳያደርሱ አይቀርም፤ ጉዳዩን በዝርዝር እየመረመርን ነው" ብለዋል።

"ከዚህ በፊት ታማኝ ናቸው የሚባሉት ግለሰቦች ከህወሓት ጋር ግንኙነት ያላቸው ስለነበሩ፤ እነሱ ናቸው እንደዚህ አይነት አካውንት እንዲከፍቱ እድሉ የሚሰጣቸው። የዚያን ጊዜ እድል ሲያገኙ አካውንት ከፍተው ይጠቀማሉ፤ ተደብቀው እዚያ ውስጥ ነበሩ፤ በዚህ አይነት መልኩ እንደዚህ አይነት ጫና ለማድረስ ጥረት ሲያደርጉ ነበር" ይላሉ የኤጀንሲው ምክትል ኃላፊ።

ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ባለቤትነቱ የግል ማኅብር ይባል እንጂ አመሰራረቱ አገሪቱን ሲያስተዳድር ከነበረው የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) ጋር ቁርኝት የነበረው ነው። አሁንም ቢሆን የሚዲያ ተቋሙ የመንግሥትን ፍላጎት የሚያንጸባርቁ ይዘቶችን ያስተላልፋል።

ዋልታ የፌስቡክ ገጹ ከቁጥጥሩ ውጪ ሲሆን ይህ የመጀመሪያው አይደለም።

ከዚህ ቀደም ያጋጠመውን ችግር በማስታወስ፤ ተመሳሳይ ችግር እንዳይከሰተ ለተቋሙ ሠራተኞች ስልጠና ተሰጥቶ እንደነበረ ከፍያለው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

"አሁን በፍጥነት የተወሰደውን አካውንት ለማስመለስ ከፌስቡክ ጋር እየተነጋገርን ነው፤ እየተሳካም ነው" ብለዋል።

አካውንቱን ጠልፈው 5000 ዶላር ከጠየቁት ጋር ምንም አይነት ንግግር እየተካሄደ አለመሆኑ እና የመንታፊዎቹ ማንነትም እስካሁን አለመለየቱ አቶ ከፍያለው ተናግረዋል።

ምክትል ኃላፊው የመንታፊዎቹ ማንነት ሲታወቅ ጉዳዩን ወደ ሕግ አካል እናደርሳለን ብለዋል።

ያጋጠመው ምን ነበር?

የዋልታን የፌስቡክ ገጽ የጠለፉት ግለሶች በፌስቡክ ገጹ ላይ ከሚያጋሩት መረጃ መረዳት እንደሚቻለው፤ የጥቃቱ ይዘት 'ራንሰምዌር' እንደሆነ መረዳ ይቻላል።

በ'ራንሰምዌር' የሳይበር ጥቃት መረጃ መንታፊዎች የኮምፒዩተር ሥርዓትን ወይም አካውንቶቹን በመጥለፍ የጠየቁት ገንዘብ እስኪሰጣቸው ድረስ ገጹን ወይም ሥርዓቱን ተቆጣጥረው ይቆያሉ።

የዋልታን የፌስቡክ ገጽን የጠለፉት መረጃ መንታፊዎች እንደሌሎቹ ክፍያ የሚጠይቁት በክሪፕቶ ከረንሲዎች ነው። በክሪፕቶ ካረንሲዎች (ዲጂታል ገንዘብ) አማካይነት ለሚፈጸም ገንዘብ የተቀባዩን ማንነት እና አድራሻ መለየት ፍጹም አዳጋች ሊሆን ይችላል።

የፌስቡክ ገጽን የጠለፉት መረጃ መንታፊዎች ገጹን ለመልቀቅ 5ሺህ ዶላር በኢቲሪያም (ETH) እንዲከፈላቸው ጠይቀዋል።

በአሁኑ ሰዓት የአንድ ኢቲሪም ዋጋ ወደ 3 ሺህ 161 የአሜሪካ ዶላር አካባቢ ነው። መረጃ መንታፊዎቹ ገጹን ለመልቀቅ 2 ኢቲሪያም እንዲከፈላቸው በዋልታ ገጽ ላይ ከፍያ የሚፈጸምበት አድራሻን ለጥፈው ነበር።