ሩሲያ በሞስኮ የሚገኘውን የዶቼ ቬለን ቢሮ መዝጋቷ ጀርመንን አስቆጣ

የዶቼ ቬለ ቢሮ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

ሩሲያ በሞስኮ የሚገኘውን የአለም አቀፉን ጣቢያ ዶቼ ቬለን ቢሮ መዝጋቷን ጀርመን እና የአውሮፓ ህብረት አወገዙ።

ሁሉም የዶቼ ቬለ ሰራተኞች የፕሬስ ፈቃዳቸውን የተነጠቁ ሲሆን የቴሌቪዥን ጣቢያውም በሩሲያ እንዳያሰራጭ ተከልክሏል።

የጀርመኑ የባህል ሚኒስትር እርምጃው "በምንም መልኩ ተቀባይነት የለውም" ብለዋል።

የጀርመን ተቆጣጣሪዎች በቀድሞ ስሙ ሩሲያ ቱዴይ (አርቲ) የሰርቢያን ፈቃድ ይጠቀማል በሚል የዘጉ ሲሆን ሩሲያ ለዚያ አጸፋ ነው ስትል ትከራከራለች።

የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ማሪያ ዛካሮቫ አርብ ዕለት ለጀርመን መንግሥት ሁለቱንም ሃገራት ሊያስማማ የሚችል የሰላም ሃሳብ ያቀረቡ ሲሆን ጀርመን "ሁኔታውን ለማስተካከል ከተንቀሳቀሰች ሩሲያም ታስተካክላለች" ሲሉ ተናግረዋል ።

አርቲ በእንግሊዝኛ፣ በፈረንሳይኛ እና በስፓኒሽ ቋንቋዎች ጣቢያዎችን የከፈተ ሲሆን በያዝነው ዓመት ታህሳስም በጀርመንኛ ቋንቋ የሳተላይት ቻናል ከአውሮፓ ህብረት ውጭ ከሆነችው የሰርቢያ ፈቃድን እየተጠቀመች ትገኛለች።

አርቲ የሩሲያ ፕሮፓጋንዳ አካል ተደርጎ የሚታይ ሲሆን የጀርመን ፈቃድ ሰጪ ባለስልጣን ዛክ በበኩሉ ጣቢያው የአውሮፖ ህብረት ፈቃድ የለውም ሲል አግዶታል። በዚህም ምክንያት ጣቢያው በቀናት ውስጥ ከአውሮፓ የሳተላይት ኔትወርክ እንዲነሳ ተደርጓል።

የዶቼ ቬለ ዋና ዳይሬክተር ፒተር ሊምበርግ ሩሲያ ቢሮውን ለመዝጋት መወሰኗ ከልክ ያለፈ ያሉት ሲሆን " ይም የሩሲያ መንግሥት ለፕሬስ ነፃነት ፍላጎት እንደሌለው ማሳያ ነው" ብለዋል።

የዶቼ ቬለ የሞስኮ ቢሮ ኃላፊ ጁሪ ሬሼቶ አርብ እለት ከጥዋቱ ሶስት ሰዓት ቢሮው ይዘጋል የሚለውን ዜና መስማታቸው እንዳስደነገጣቸውና "ያልተመለሱ በርካታ ቴክኒካዊ እና ህጋዊ ጥያቄዎች አሉ። እስካሁን ድረስ የምናውቀው የፕሬስ ፈቃዳችንን መመለሳችንን ብቻ ነው" ብለዋል።

የባህል ሚኒስሯ ክላውዲያ ሮት ሩሲያ የአርቲን የፈቃድ ችግር "ፖለቲካዊ ምላሽ ለመስጠት ያላግባብ እንዳይጠቀሙበት" ጥሪ አቅርበዋል።

አርቲ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ጣቢያውም ላይ ችግሮች አጋጥመውታል። የዩናይትድ ኪንግደም ተቆጣጣሪ ኦፍኮም "አድሎአዊነትን አሳይቷል" በሚል 200 ሺህ ፓውንድ ቅጣት ጥሎበታል።

ሌሎች የጀርመን ሚዲያዎች ለዶቼ ቬለ ድጋፋቸውን የሰጡ ሲሆን የጀርመን የጋዜጠኞች ፌዴሬሽን እገዳው በአስቸኳይ እንዲነሳ ጠይቋል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ የላቲቪያ ፍትህ ሚኒስትር ዲ ደብሊው (ዶቼ ቬለ) ቢሮውን ወደ መዲናዋ ሪጋ ለማዘዋወር ፈቃድ እሰጣለሁ ብሏል።

የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዶቼ ቬለን "የውጭ አገራት ወኪል" ብሎ ለመፈረጅ አሰራር መጀመሩም የተገለጸ ሲሆን ይህ ቃልም በሶቭየት የፖለቲካ ተቃዋሚዎችን ለማጥቃት የሚጠቀሙበት አገላለፅ ነው።

በቅርብ ወራት ውስጥ የሩሲያ ባለስልጣናት ጋዜጠኞች አባርረዋል እንዲሁም ተቋማትን ዘግተዋል።

የቢቢሲ የሩሲያ ዘጋቢ አንድሬ ዛካሮቭ ባለፈው አመት "የውጪ ወኪል" ተብሎ የተፈረጀ ሲሆን ሌላኛዋ የቢቢሲ ጋዜጠኛ ሳራ ራይንስፎርድ እና ሆላንዳዊ ጋዜጠኛ ቶም ቬኒንክ ተባረዋል።

ከሩሲያ ጥንታዊ የሲቪል መብቶች ድርጅቶች አንዱ የሆነው 'ሜሞሪያል' (መታሰቢያ) ተዘግቷል።