የአፍሪካ ዋንጫ አዘጋጅ ካሜሩን በሶስተኛነት አጠናቀቀች

የካሜሩን ተጫዋቾች

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል

የአፍሪካ ዋንጫ አዘጋጅ ካሜሩን በትናንትናው ዕለት ጥር 28፣ 2014 ዓ.ም በተካሄደው ጨዋታ በፍፁም ቅጣት ምት ቡርኪናፋሶን በመርታት ሶስተኛ ሆና አጠናቃለች።

ካሜሩን በቡርኪናፋሶ 3ለ0 እየተመራች የነበረ ቢሆንም በኋላ ግን 3 ጎል በማስቆጠር እኩል በመሆናቸው ጨዋታው በፍፁም ቅጣት እንዲጠናቀቅ ሆኗል። በዚህም ካሜሩን አሸናፊ ሆናለች።

ቡርኪናፋሶ በስቲቭ ያጎ፣ የካሜሩኑ አንድሬ ኦናና በራሱ ላይ ባስቆጠራት ግብ እንዲሁም በጅብሪል ኦታራ ጎሎች 3 ለ0 እየመራች ነበር።

ነገር ግን በደጋፊዎቻቸው ፊት የተጫወቱት ካሜሮኖች በስቴፋን ባሆከንና በቪንሰንት አቡበከር ሁለት ጎሎች ወደ መጨረሻው ሰዓት እኩል መሆን ችለዋል።

የጨዋታው 90 ደቂቃ ከተጠናቀቀ በኋላ ተጨማሪ ጊዜ ሳይጨመር ቡድኖቹ በፍፁም ቅጣት ምት እንዲለያዩ ተደርጓል።

ለ49 ደቂቃዎች ያህል ጨዋታውን ተቆጣጥረውት ለነበረው ቡርኪናፋሶዎች ውጤቱ አሳዛኝ ሆኗል።

በተቃራኒው አምስት ጊዜ የአፍሪካ ዋንጫ አሸናፊዋ ካሜሩን አምስቱንም የቅጣት ምቶች ወደ ጎል በመቀየር ግሩም በሆነ መልኩ በሶስተኛነት አጠናቃለች።

በዛሬው ዕለት የአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታ የሚጠናቀቅ ሲሆን የሰባት ጊዜ ሻምፒዮናዋና ክብረ ወሰንን የጨበጠችው ግብፅ የፍፃሜ ጨዋታዋን ከሴኔጋል ጋር ታደርጋለች።