ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ማሊ መፈንቅለ መንግሥት፡ የማሊ ወታደራዊ መሪዎች የፈረንሳይ አምባሳደር አገሪቷን ለቀው እንዲወጡ አዘዙ
የማሊ ወታደራዊ መሪዎች የፈረንሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በሽግግር መንግሥቱ ላይ የሰጡትን አስተያየት ተከትሎ የአገሪቷን አምባሳደር አባረሩ።
ፈረንሳይ ከማሊ እንዲወጡ 72 ሰዓት ለተሰጣቸው አምባሳደሯ ጆል ሜየር ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ትዕዛዝ ሰጥታለች።
የፈረንሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጂን ይቭስ ሊ ድሪያን ባለፈው ሳምንት በማሊ መፈንቅለ መንግሥት ያካሄደው ወታደራዊ ኃይል "ሕገ ወጥ እና ከቁጥጥር ውጭ የሆነ ነው" ሲሉ ተናግረው ነበር።
የምዕራብ ኃያላን አገራት ሩሲያ የፈረንሳይ ቅኝ ግዛት በነበረችው ማሊ ውስጥ የምታደርገው ተሳትፎ እያደገ መምጣቱም አሳስቧቸዋል።
ሞስኮ የአካባቢው የጸጥታ ኃይሎች ከጂሃዲስት አማጺያን ጋር የሚያደርጉትን ውጊያ ለማጠናከር ከቅርብ ሳምንታት በፊት ወታደራዊ አማካሪዎችን ልካለች።
በመቶዎች የሚቆጠሩ የሩሲያ የሰለጠኑ ወታደሮችም በአገሪቷ ውስጥ እየሠሩ መሆናቸውን ያልተረጋገጡ ሪፖርቶች አመልክተዋል።
እአአ በ2013 የማሊ መንግሥት በጂሃዲስቶች ላይ የሚወስደውን እርምጃ ለመደገፍ ጣልቃ የገባችው ፈረንሳይ ግን ወታደሮቿን ለመቀነስ አቅዳለች።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሊ ድሪያን በሰጡት ሌላ ቃለ ምልልሳቸው የሩሲያ ወታደሮች " ወታደራዊውን መንግሥት ለመጠበቅ በምላሹ የአገሪቷ ሃብት እየበዘበዙ ነው" ሲሉ ከሰዋል።
በፈረንሳይ እና የባህር በር በሌላትና በዓለም ድሃ ከሆኑት አገራት አንዷ በሆነችው ምዕራብ አፍሪካዊቷ አገር ማሊ መካከል ያለው ግንኙነት ወታደራዊ ኃይሉ ነሐሴ ወር 2020 ላይ ሥልጣን ከተቆጣጠረ ወዲህ እየሻከረ መጥቷል።
በተለይ በዚህ ወር ወታደራዊ ኃይሉ በየካቲት ወር ምርጫ ለማካሄድ የተደረሰውን ስምምነት በመሻር እስከ 2025 ሥልጣን ላይ እንደሚቆይ ቃል መግባቱን ተከትሎ በአገራቱ መካከል ያለው ውጥረት አይሏል።
የፈረንሳይ መከላከያ ሚኒስትር ፍሎረንስ ፓርሊ የማሊ መሪዎች በአገራቸው ላይ " ቀውስን" እየጨመሩ ነው ሲሉ ከሰዋል።
የማሊ መንግሥት በብሔራዊ ቴሌቪዥን በሰጠው መግለጫ ላይ "በቅርቡ የፈረንሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የሰጡትን የጥላቻ እና ያልተገቡ አስተያየቶች ተከትሎ አምባሳደሩ በ72 ሰዓታት ውስጥ አገሪቷን ለቀው እንዲወጡ የተላለፈውን ውሳኔ እንዲያውቁት መደረጉን አስታውቋል።
የፈረንሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም ከዚያ በኋላ አምባሳደሩን መጥራቱን አረጋግጧል።
ፈረንሳይ እአአ በ2013 ማሊ የገባችው እስላማዊ ታጣቂዎች የሰሜኑን ክፍል ከያዙ በኋላ ነው። በፈረንሳይ እርዳታም የማሊ ጦር ግዛቱን ማስመለስ ችሏል። ይሁን እንጂ ታጣቂዎቹ በሳህል አካባቢ የሚፈጽሙት ደም አፋሳሽ ጥቃት እየጨመረ ነው።
ፈረንሳይ በኒጀር እና በቡርኪና ፋሶ ወታደሮች ያሏት ሲሆን የጂሃዲስት አማጺያንን እየተዋጉ ነው።