በጀርመን ሁለት የፖሊስ መኮንኖችን የገደለው ግለሰብ በፖሊስ እየታደነ ነው

ፖሊሶች

የፎቶው ባለመብት, EPA

ታትሟል

በምዕራባዊ የጀርመን ግዛት ውስጥ በመደበኛ የትራፊክ ቁጥጥር ሥራ ላይ የነበሩ ሁለት የፖሊስ መኮንኖች ተገደሉ። ፖሊስ ገዳዩን ለመያዝ አሰሳ ላይ ነው።

የፖሊስ መኮንኖቹ ከፈረንሳይ ድንበር ጋር በሚዋሰነው ራይንላንድ ፓለቲኔት ግዛት ኩሴል አካባቢ ሰኞ ከሰዓት በኋላ አንድ ተሽከርካሪ አስቁመው ነበር።

የ29 ዓመቱ እና የ24 ዓመቷ የፖሊስ መኮንኖች እዚያው ቦታው ላይ እያሉ በተተኮሰባቸው ጥይት ተገድለዋል። ሴቷ የፖሊስ መኮንን በፖሊስ አካዳሚ ተማሪ ነበረች።

ፖሊስ ግድያውን የፈፀመውን ግለሰብ እያደነ ነው።

ከግድያው በኋላ በአካባቢው ያሉ መንገዶች የተዘጉ ሲሆን ባለሥልጣናት ሰዎች በነጻ ባገኙትና ደኅንነቱ ባልተጠበቀ ተሽከርካሪ ላይ እንዳይሳፈሩ አሳስበዋል።

ፖሊስ ግለሰቡን አድኖ ለመያዝ ፍለጋውን ወደ ጎረቤት ግዛት ሳርላንድ አስፋፍቷል።

ስለግድያው ዝርዝር ሁኔታ እስካሁን አልተገለጸም።

ጥቃቱን ስላደረሰው ግለሰብ፣ ስለ ተሽከርካሪው ወይም ወደየት አቅጣጫ እንዳመለጠ የተባለም ነገር የለም። የግድያውን ምክንያት ምን ሊሆን እንደሚችልም ፖሊስ የሰጠው አስተያየት የለም።

የጀርመን ጋዜጣ -ቢልድ የፖሊስ መኮንኖቹ ሁለት የራዲዮ መልዕክቶችን አስተላልፈው እንደነበር ዘግቧል።

መጀመሪያ ላይ የፖሊስ መኮንኖቹ አንድ አጠራጣሪ መኪና አስቁመው በመኪና እቃ መጫኛ ውስጥ የግድያ ወንጀልን ያበረታታል በሚል ክልከላ የተጣለበት ጌም ማግኘታቸውን ተናግረዋል ብሏል ጋዜጣው።

ከዚያም ብዙም ሳይቆይ "ሊተኩሱብን ነው!" ሲሉ የራዲዮ መስመሩ ከመቋረጡ በፊት ሁለተኛውን መልዕክት ማስተላለፋቸውን ጋዜጣው አስነብቧል።

በወቅቱ ተጨማሪ ኃይል በቦታው ቢደርስም ሴቷ የፖሊስ መኮንን ከመድረሳቸው በፊት ሕይወቷ ማለፉን የአገሪቷ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል። ከዚያም የሥራ ባልደረባዋ ከእርሷ በኋላ ሕይወቱ አልፏል።

የፖሊስ ማኅበር ሊቀመንበር የሆኑት ሳብሪና ኩንዝ በተፈጠረው ነገር ማዘናቸውን ገልጸው፤ የሟች ቤተሰቦች፣ ዘመዶችና የሥራ ባልደረቦችን እንደሚያስቧቸው ገልጸዋል።

"በሁሉም የፖሊስ መኮንኖች እውነተኛ ቅዠት ውስጥ እየኖርን ነው" ሲሉም በተፈጠረው ነገር መደናገጣቸውን ተናግረዋል።