ዩክሬን ፡ ዩኬ በዩክሬን ያለውን ውጥረት ተከትሎ በርካታ ወታደሮችን ለማሰማራት እያሰበች ነው

ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰንና የመከላከያ ዋና አዛዥ አድሚራል ሰር ቶኒ ራዳኪን

የፎቶው ባለመብት, ANDREW PARSONS/NO 10

የምስሉ መግለጫ, ባለፈው ረቡዕ ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ስላሉት አማራጮች በመከላከያ ዋና አዛዥ አድሚራል ሰር ቶኒ ራዳኪን ገለጻ ተደርጎላቸዋል።
ታትሟል

ዩናይትድ ኪንግደም በምሥራቅ አውሮፓ የምታሰማራውን ወታደሮቿን በእጥፍ ለማሳደግ እያሰበች መሆኑ ተገለጸ።

ይህ የተሰማው ሚኒስትሮች በዩክሬን ላይ ከፍተኛ ውጥረት በነገሰበት ወቅት ሩሲያ ላይ ጫና ለማሳደር አማራጮችን እያሰላሰሉ ባሉበት ወቅት ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ወታደሮችን ለማሰማራት መታሰቡ "ለክሬምሊን ግልጽ መልእክት ያስተላልፋል" ብለዋል።

በሌላ በኩል የመከላከያ እና የውጭ ጉዳይ ኃላፊዎች ውጥረቱን ለማርገብ በሞስኮ ከሚገኙ አቻዎቻቸው ጋር ለመገናኘት በዝግጅት ላይ ናቸው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስም በቀጣይ ቀናት ከሩሲያው ፕሬዚደንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር በስልክ ይወያያሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በዚህ ሳምንት ምሥራቅ አውሮፓን የሚጎበኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ዩኬ "የሩሲያን የጥፋት እንቅስቃሴ እንደማትታገስ" እና ሁል ጊዜም ከሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃልኪዳን ድርጅት [ኔቶ] አጋሮቻቸው ጋር እንደሚቆሙ ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጨምረውም ፕሬዚደንት ፑቲን የደም መፋሰስ እና የጥፋት መንገድን ከመረጡ ለአውሮፓ አሳዛኝ ነው የሚሆነው። ዩክሬን የራሷን መጻኢ እድል ለመምረጥ ነጻ መሆን አለባት " ብለዋል።

" የኔቶ አጋሮቻችንን በየብስ፣ በባህር እና በአየር ለመደገፍ ወታደሮቻችን በሚቀጥለው ሳምንት በአውሮፓ ለመሰማራት እንዲዘጋጁ ትዕዛዝ ሰጥቻለሁ" ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ።

ሩሲያ በዩክሬን ድንበር አቅራቢያ 100 ሺህ ወታደሮችን፣ ታንኮችን፣ ከባድ መሳሪያዎችን እና ሚሳይሎችን አስፍራለች።

ይሁን እንጂ ከአውሮፓ እና ከሩሲያ ጋር የምትዋሰነውን የቀድሞዋን ሶቭየት ሪፐብሊክ ለመውረር አቅዳለች መባሉን አስተባብላለች።

ዩናይትድ ኪንግደም በኢስቶኒያ የሰፈሩ ከ900 በላይ የጦር መኮንኖች ያሏት ሲሆን ከ100 በላይ የሚሆኑት ለሥልጠና ተልዕኮ ዩክሬን ይገኛሉ። 150 የሚጠጉ የጦር ፈረሰኞች ቡድን ደግሞ ወደ ፖላንድ ተሰማርቷል።

የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ሰኞ ዕለት በሩሲያ ስትራቴጂያዊ እና የፋይናንስ ፍላጎቶች ላይ ጠንካራ ማዕቀብ ላይ ፓርላማው ያሳለፈውን ውሳኔ ያሳውቃል ተብሎ ይጠበቃል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የዩናይትድ ኪንግደም ባለሥልጣናት አገሪቷ ያቀረበችው ሃሳብ በዝርዝር ተነጋግሮ ለመቋጨት ወደ ብራስልስ ያቀናሉ ተብሏል።