ዴንማርክ በምዕራብ አፍሪካዊቷ አገር ጥያቄ ጦሯን ከማሊ ልታስወጣ ነው

ታትሟል

ዴንማርክ በማሊ ወታደራዊ የሽግግር መንግሥት ጥያቄ ጦሯን ከምዕራብ አፍሪካዊቷ አገር ማሊ ማስወጣት እንደምትጀምር አስታወቀች።

የሽግግር መንግሥቱ ዴንማርክ በማሊ ያላትን ጦር በአስቸኳይ እንድታስወጣ በዚህ ሳምንት ጠይቆ ነበር።

የፈረንሳይ እና የአውሮፓ ጥምር ኃይሎች የዴንማርክ ጦር በማሊ እንዲቆይ የማሊን የሽግግር መንግሥት ሲወተውቱ ቆይተዋል።

የማሊ የሽግግር መንግሥት ግን ረቡዕ ጥር 17/2014 ዓ.ም የዴንማርክ ጦር በማሊ እንዲቆይ በአገሪቱ መንግሥት የተሰጠ ፍቃድ የለም በማለት አውሮፓዊው ጦር አገር ለቆ እንዲወጣ ጠይቋል።

የሽግግር መንግሥቱ ጥያቄ የተሰማው ማሊ ከቅኝ ገዢዋ ፈረንሳይ ጨምሮ ከአውሮፓ አገራት ጋር ያላት ግንኙነት ከተቀዛቀዘ በኋላ ነው።

ይህን ተከትሎ የዴንማርክ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ጄፔ ኮፎድ ትናንት ሐሙስ ጥር 18/2014 ዓ.ም የዴንማርክ ጦር ከማሊ በፍጥነት እንደሚወጣ ይፋ አድርገዋል።

ዴንማርክ ቀድሞውኑ ጦሯን ወደ ማሊ የላከችው በአገሪቱ መንግሥት ግብዣ ነበር። የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ፤ "የዴንማርክ ድጋፍ ከአገሪቱ ይወጣል" ብለዋል።

ከ10 ቀናት በፊት ዴንማርክ በማሊ የሚንቀሳቀሱ እስላማዊ ታጣቂዎችን ለመዋጋት የሚደረገውን ጥረት ለመደገፍ 105 የጦር አባላትን ልካ ነበር።

የአውሮፓ አገራት 'ታኩባ' የተሰኘ ልዩ ኃይል መስርተው እስላማዊ ታጣቂዎችን ለመግታት በማሊ ሰፍረዋል። ፈረንሳይ፣ ዴንማርክ፣ ፖርቹጋል፣ ቤልጂዬም፣ ኢስቶኒያ እና ኔዘርላንድስ የዚህ ጥምር ኃይል አባል አገራት ናቸው።

ይህን ጥምር ኃይል የምትመራው ፈረንሳይ የዴንማርክ ጦር ከማሊ መውጣቱ አላስደሰታትም።

ሰኔ 2013 ዓ.ም ላይ በመፈንቅለ መንግሥት ስልጣን ላይ የወጣው ጦር፤ በቀጣይ ወር ምርጫ ለማካሄድ ቃል ገብቷል።