ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የት እንዳለ ሳይታወቅ የቆየው ጋዜጠኛ ክብሮም ወርቁ በአባ ሳሙኤል ማቆያ ታስሮ እንደነበር ተናገረ
ከሁለት ወራት በላይ ያለበት ሳይታወቅ የቆየው ጋዜጠኛ ክብሮም ወርቁ ዛሬ ጥር 18/2014 ዓ.ም ታስሮ ከቆየበት የአባ ሳሙኤል ማቆያ መፈታቱን ጋዜጠኛው ከቢቢሲ ጋር ባደረገው አጭር ቆይታ አረጋገጠ።
ከጥቅምት 16/2014 ዓ.ም ጀምሮ በቁጥጥር ስር የዋለው በአሃዱ ራዲዮ የዜና ክፍል አዘጋጅ የነበረው ጋዜጠኛ ክብሮም ፖሊስ ብሎም ቤተሰቡ ያለበትን አናውቅም ማለት የጀመሩት ከኅዳር 09/2014 ጀምሮ ነበር።
ክብሮም በአሃዱ ራዲዮ ላይ በሚያቀርበው የመዝናኛ ፕሮግራሞች የሚታወቅ ሲሆን "ሁከት እና ብጥብጥ በማነሳሳት" ወንጀል ተጠርጥሮ ነበር በወርሃ ጥቅምት በቁጥጥር ስር የዋለው።
ጋዜጠኛው ለእስር የታዳረገው በራዲዮ ጣቢያው የሐይቅ ከተማ በህወሓት ታጣቂዎች ቁጥጥር ስር ውላለች የሚል ዘገባ መሰራቱን ተከትሎ መሆኑ ይታወሳል።
"ፍርድ ቤት በነጻ ካሰናበተኝ በኋላ በድጋሚ የታሰርኩት። በመኪና ይዘውኝ ሲሄዱ ወዴት ይዘውኝ እንደሚሄዱ አላውቅም ነበር። እሱ ጭንቀት እና መረጋጋት ፈጥሮብኝ ነበር። በኋላ ግን እንደማንኛውም ተጠርጣሪ ነው የቆየሁት" ሲል ክብሮም ለቢቢሲ ተናግሯል።
ለበርካታ ሳምንታትም ቤተሰቦቹ የት እንዳለ ካለማወቃቸው በተጨማሪ ጥየቃ ሳይፈቀድ መቆየቱ የእስር ቤት ቆይታውን ከባድ እንዳደረገበት ክብሮም ተናግሯል። አክሎም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በእስር ቤቱ የህክምና እና የምግብ ችግር እንደነበረ ገልጿል።
"ጋዜጠኝነት አፍቅሬ የምሰራው ሥራ ስለሆነ መስራቴን እቀጥላለሁ። በግሌ ዋጋ የሚያስከፍል ቢሆንም ሙያዊ ሥነምግባሬን ጠብቄ መስራቴን እቀጥላለሁ" በማለት ወደ ጋዜጠኝነት ሥራው እንደሚመለስ ክብሮም ተናግሯል።
ክብሮም መጀመሪያ ታስሮ የነበረው በተለምዶ ሦስተኛ የሚባለው የአዲስ አበባ ፖሊስ የነበረ ሲሆን፣ በወቅቱ ጥየቃ እንደሚፈቀድ ብሎም ከሩቅ ሰላምታ እንደሚለዋወጡና ምግብ ሲያቀብሉት እንደነበር ወላጅ አባቱ አቶ ወርቁ ለቢቢሲ መናገራቸው ይታወሳል።
ኅዳር 09/2014 ዓ.ም ነበር ፍርድ ቤት በ15 ሺህ ብር ዋስትና ክብሮም እንዲለቀቅ የወሰነው።
ወላጅ አባቱም አስፈላጊውን የዋስትና ገንዘብ ከፍለው ለአንድ ሳምንት ያህል ይፈታል ብለው ቢጠብቁም ባለመፈታቱ ለችሎት መማልከታቸውን ቀጥሎም ፖሊስ ይግባኝ በመጠየቁ በእስር መቆየቱን ይታወሳል።
ክብሮም ያለበት ያለመታወቁን ተከትሎ ቤተሰቦቹ አካልን ነጻ የማውጣት ክስ መስርተው ክሱ በተለያዩ የይግባኝ ሂደቶች ውስጥ ማለፉም አይዘነጋም።
የሚኒስትሮች ምክር ቤት ዛሬ እንዲነሳ የወሰነው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በመላው አገሪቱ ከተደነገገ በኋላ ክብሮም ወርቁን ጨምሮ በርካታ ጋዜጠኞች ለአስር ተዳርገዋል።
የተወሰኑት ባለፉት ሳምንታት የተፈቱ ሲሆን ሌሌች አሁንም በአስር ላይ እንደሚገኙ ይታወቃል።