የቡርኪናፋሶ ጦር ሥልጣን መቆጣጠሩን አስታወቀ

ፕሬዚደንት ሮክ ካቦሬን

የፎቶው ባለመብት, AFP

ታትሟል

የቡርኪናፋሶ ወታደራዊ ኃይል ሥልጣን መቆጣጠሩንና ፕሬዚደንት ሮክ ካቦሬን ከሥልጣን ማስወገዱን አስታወቀ።

ጦሩ ይህንን ያስታወቀው የጦሩ መኮንን በመንግሥት የቴሌቪዥን ጣቢያ በሰጡት መግለጫ ሲሆን ወታደራዊው ኃይሉ ሥልጣን የተቆጣጠረው በአገሪቷ ያለው የጸጥታ ችግር እየከፋ በመምጣቱ እንደሆነ ገልጸዋል።

ፕሬዚደንት ካቦሬ የእስላማዊ ታጣቂዎችን አመጽ ለማስቆም ባለመቻላቸው ተቃውሞ ገጥሟቸው ነበር።

አሁን ላይ ፕሬዚደንቱ የት እንዳሉ ግልጽ አይደለም። ይሁን እንጂ የጦር መኮንኑ በቁጥጥር ሥር የዋሉ ሁሉም ሰዎች ደኅንነቱ በተጠበቀ ቦታ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

በአገሪቷ መፈንቅለ መንግሥቱ የተካሄደው ወታደሮች የጦር ካምፑን ከተቆጣጠሩ ከአንድ ቀን በኋላ ሲሆን በዋና መዲናዋ ኦጋድጉም ተኩስ ነበር።

ቀደም ብሎ ገዥው ፓርቲ ፒፕል ሙቭመንት ፎር ፕሮግረስ (ፒኤምፒ) ፕሬዚደንት ካቦሬ እና አንድ ሌላ የመንግሥት ሚኒስትር ከግድያ ሙከራ መትረፋቸውን ገልጾ ነበር።

እሁድ እለት አማጺ ወታደሮች ከእስላማዊ መንግሥት (አይኤስ) ቡድን እና ከአልቃይዳ ጋር ግንኙነት ያላቸው ታጣቂዎችን ለመዋጋት ወታደራዊ አዛዦች ከሥልጣን እንዲለቁና ተጨማሪ ተጨማሪ ሃብት እንዲመደብላቸው ሲጠይቁ ነበር።

ጦሩ በመግለጫው ካቦሬ አገሪቷን አንድ ማድረግ እና "የአገሪቷን መሠረት አደጋ ላይ የሚጥለውን" የጸጥታ ቀውስ መፍታት አልቻሉም ብሏል።

መግለጫው የወጣው ከዚህ ቀደም ተሰምቶ በማይታወቅ ዘ ፓትሪዎቲክ ሙቭመንት ፎር ሴፍጋርድ ኤንድ ሪስቶሬሽን ( ኤምፒኤስአር) በተሰኘ ቡድን ስም ነው።

መግለጫው በሌላ የጦር መኮንን ቢነበብም የተፈረመው ግን የመፈንቅለ መንግሥቱ መሪ እንደሆኑ በሚታመነው በሌተናንት ኮሎኔል ፖል ሄንሪ ሳንዳጎ ዳሚባ እና እስላማዊ ታጣቂዎችን በመዋጋትም የዓመታት ልምድ ባላቸው ኮማንደር ነው።

የአገሪቷ ምክር ቤቱ እና መንግሥት እንደተበተነና ሕገ መንግሥቱም እንደታገደ በመግለጫው ተመልክቷል። ይሁን እንጂ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓትን ለመመለስ ቃል ገብተዋል።

ጦሩ አክሎም የቡርኪና ፋሶ ድንበር መዘጋቱንም በመግለጫው አስታውቋል። በአገሪቷ የሞባይል ኢንተርኔት አገልግሎትም ተቋርጧል።

የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ መፈንቅለ መንግሥቱን አውግዘው ጦሩ ለፕሬዝንደንት ካቦሬ ጥበቃ እንዲደረግላቸው እና አካላዊ ደኅንነታቸውን እንዲያረጋግጥ ጠይቀዋል።

የአፍሪካ ሕብረት እና የምዕራብ አፍሪካ አገራት የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ (ኢኮዋስ) በበኩሉ በኃይል ሥልጣን መቆጣጠሩን አውግዘዋል።

ኢኮዋስ አክሎም ወታደሮቹ ከሥልጣን ለተነሱት ፕሬዚደንት ደኅንነት ተጠያቂ ናቸው ብሏል።

ጥቂት ስለቡርኪናፋሶ

  • የቀድሞዋ የፈረንሳይ ቅኝ ግዛት ቡርኪናፋሶ እአአ በ1960 ነፃነቷን ካገኘች በኋላ በርካታ መፈንቅለ መንግሥቶችን ጨምሮ የከፋ አለመረጋጋትም አጋጥሟታል።
  • አገሪቷ 'የታማኝ ሰዎች ምድር' የሚል ትርጉም ያለውን 'ቡርኪና ፋሶ ' የተሰኘውን ሥም ያገኘችው እአአ በ1983 ሥልጣን በተረከበው አብዮታዊ ወታደራዊ መኮንን ቶማስ ሳንካራ ነው። ቶማስ ሳንካራ እአአ በ1987 ከሥልጣን ተወግዶ ተገድሏል።
  • እአአ ከ2015 ጀምሮ ደግሞ አገሪቷ ከጎረቤት ማሊ የተስፋፋውን የእስላማዊ ታጣቂ ቡድን እየተዋጋች ነው። ይህም በሠራዊቱ ውስጥ ቁጣን የቀሰቀሰ ሲሆን ወሳኝ የሆነውን የቱሪዝም ኢንዱስትሪም ክፉኛ ጎድቷል።