የቡርኪና ፋሶው ፕሬዝደንት ባመጹ ወታደሮች ቁጥጥር ሥር መዋላቸው ተዘገበ

የቡርኪና ፋሶ ፕሬዝደንት ሮች ካቦሬ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, የቡርኪና ፋሶ ፕሬዝደንት ሮች ካቦሬ
ታትሟል

የቡርኪና ፋሶው ፕሬዝደንት ሮች ካቦሬ ባመጹ የአገሪቱ ጦር ኃይል ወታደሮች በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ተዘገበ።

ቁጥራቸው አነስተኛ የሆኑ የምዕራብ አፍሪካዊቷ አገር ወታደሮች እና ከፍተኛ የጦር አመራሮች ከሥራቸው እንዲሰናበቱ እና ጽንፈኛ እስላማዊ ታጣቂዎችን ለመዋጋት ተጨማሪ ሃብት እንዲመደብላቸው ሲጠይቁ ነበር።

የአገሪቱ ጦር አባላት የአገሪቱን ብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያን ዋና መሥሪያ ቤት ከበው ይዘዋል።

የአገሪቱ መንግሥት ግን ቀውሱ በቁጥጥር ሥር መዋሉን አስታውቆ፤ የፕሬዝደንቱን በወታደሮች ቁጥጥር ሥር ውለዋል እና መፈንቅለ መንግሥት ተፈጽሟል መባሉን አስተባብሏል።

የወታደሮች አመጽ እየተሰማ ባለበት ጊዜ ምሽት ላይ በፕሬዝዳንቱ ቤተ መንግሥት አቅራቢያ የተኩስ ድምጽ ሲሰማ ነበር።

በመቶዎች የሚቆጠሩ ሲቪሎች ወታደሮቹን ለመደገፍ ወደ አደባባይ መውጣታቸውን ተከትሎም የአገሪቱ ባለሥልጣናት የሰዓት እላፊ አውጀዋል።

የሰሞኑ ቀውስም እ.አ.አ. ከ2015 ጀምሮ ምዕራብ አፍሪካን በማውደም ላይ የሚገኘውን አክራሪ እስላማዊ ቡድን ለማስቆም ባለመቻሉ የፕሬዝዳንት ሮክ ካቦሬ መንግሥት ላይ የሚቀርበው ቅሬታ ማደጉን የሚያሳይ ምልክት ነው።

እ.አ.አ. በ2015 በመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ የተከሰሱ ወታደሮች በምዕራባዊ የአገሪቱ ክፍል በሚገኘው ሳንጎውሌ ላሚዛና ተብሎ በሚጠራው ካምፕ ውስጥ በእስር ላይ ይገኛሉ።

በሰሜን ካያ እና ኡዋሂጉያ በሚገኙ ወታደራዊ ካምፖችም የተኩስ ድምጽ ይሰማ እንደነበር የአሜሪካ ኤምባሲ አስታውቋል። ወታደሮቹ የሠራዊቱ ዋና አዛዥ እና የስለላ አገልግሎት ኃላፊ ከሥራ እንዲባረሩ ጠይቀዋል።

አክራሪ ኃይሎቹን ለመዋጋት ወደ ጦር ግንባር ተጨማሪ ወታደሮች እንዲሰማሩ፣ ለቆሰሉ እና በጦርነት ለተገደሉት ወታደሮች ቤተሰቦች የተሻለ እንክብካቤ እንዲደረግ የሚለውን ጨምሮ በርካታ ጥያቄዎችን አቅርበዋል።

የቡርኪና ፋሶ የመከላከያ ሚኒስትር ባርትሄሌሚ ሲምፖሬ በአገሪቱ ቴሌቪዢን ቀርበው "በየአካባቢው የተገደቡ እና የጥቂት ሰፈሮች" ክስተቶች ናቸው ሲሉ ሁኔታውን ያስተባበሉ ሲሆን የትኛውም "የሪፐብሊካን ተቋም" ኢላማ እንዳልሆነ ተናግረዋል።

ጄኔራል ሲምፖሬ መንግሥት ተጨማሪ መረጃዎችን በጊዜው ይፋ እንደሚያደርግ በመግለጽ ሰዎች የዕለት ለዕለት ተግባራቸውን እንዲቀጥሉ አሳስበዋል።

የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ካቦሬ የሚገኙበት ቦታ ግልጽ ባይሆንም የመከላከያ ሚኒስትሩ በቁጥጥር ሥር ናቸው ተብሎ በማኅበራዊ ሚዲያ የተናፈሰውን መረጃ አስተባብለዋል።

የኢንተርኔት ግልጋሎት ሁኔታን የሚከታተለው ቡድን ኔትብሎክስ በቡርኪና ፋሶ ኢንተርኔት አገልግሎት መስተጓጎሉን ገልጿል።