በናይጄሪያ የአምስት ዓመቷ ህጻን ግድያ ከፍተኛ ቁጣን ቀሰቀሰ

ሃኒፋ አቡበከር

የፎቶው ባለመብት, Hanifa Abubakar's family

ታትሟል

የአምስት ዓመቷ ህፃን ሃኒፋ አቡበከር ተገድላና አስከሬኗ በስብሶ መገኘቱ በናይጄሪያውያን ዘንድ ከፍተኛ ድንጋጤ እና ቁጣን ቀሰቀሰ።

በርካቶችም በማህበራዊ ትስስር ገፆች ፍትህ ለሃኒፋ እያሉም በመጠየቅ ላይ ናቸው።

ህፃኗ የምትማርበት ትምህርት ቤት ባለቤት አብዱልማሊክ መሃመድ ታንኮ በቁጥጥር ስር የዋለ ሲሆን ተቋሙም ተዘግቷል።

ግለሰቡ ሃኒፋን በታህሳስ ወር ላይ ካኖ በተባለችው ግዛት አግቷት እንደነበርና 14 ሺህ 600 ዶላር እንዲሰጠውም ጠይቆ ነበር ተብሏል።

ፖሊስ እንደገለጸው ሃኒፋ የግለሰቡን ማንነት ማወቋን ተከትሎ ገድሏታል ብሏል።

እንደ ባለስልጣናቱ ገለጻ የ34 ዓመቱ አብዱልማሊክ የህፃኗን አስከሬን በትምህርት ቤቱ ውስጥ የቀበረበትን ጥልቀት የሌለው የመቃብር ስፍራም መርቶ አሳይቷል።

አስከሬኗ ተቆፍሮ ከወጣ በኋላ የህክምና ምርመራ ተደርጎ በቤተሰቦቿም አማካኝነት የቀብር ስነስርአቷ ተፈጽሟል።

አብዱልማሊክ እስካሁን አልተከሰሱም።

ሀኒፋ ትማርበት ከነበረው የእስልምና ትምህርት ቤት ውጭ በታህሳስ ወር መጀመሪያ ላይ ነው ታግታ የተወሰደችው።

በሃኒፋ ግድያ ሌሎች ሁለት ተጠርጣሪዎችም በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ፖሊስ ገልጿል።

የህጻኗ አባት አቡበከር አብዱሰላም "ቤተሰቦቿ በከፍተኛ ስቃይ ውስጥ መውደቃቸውን" ኃዘን በሰበረው ድምፅ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የሀኒፋ እና ራሷን ስታ በመውደቋ በአሁኑ ወቅት በሆስፒታል ውስጥ እንደምትገኝም አስረድተዋል።

አባትየው ለልጃቸው ፍትህ እንዲሰጣቸው ባለስልጣናቱን ጠይቀዋል።

የካኖ ግዛት የትምህርት ኮሚሽነር ሳኑሲ ሳኢዱ ኪሩ ጠለፋውን እምነትን ማጉደል ሲሉ ገልፀውታል።

ናይጄሪያ ለገንዘብ ተብሎ በሚደረጉ አፈናዎች በከፍተኛ ሁኔታ መጨመር ጋር እየታገለች ትገኛለች። በተለይም ታጣቂ ቡድኖች በጅምላ ጠለፋዎችን ለማካሄድ ትምህርት ቤቶች ላይ ያነጣጥራሉም ተብሏል።