በዩናይትድ ኪንግደም ብዙ አይዘልቁም ተብለው የነበሩት ጥንዶች ትዳር 81 ዓመት ሞላው

ጥንዶቹ ሮን እና ጆይስ

የፎቶው ባለመብት, EXTRA CARE

ታትሟል

በዩናይትድ ኪንግደም ከለንደን 80 ኪሎ ሜትር ርቃ በምትገኘው ሚልተን ኬይንስ ከተማ የሚኖሩት ጥንዶቹ ሮን እና ጆይስ ቦንድ የ81ኛ ዓመት የጋብቻ በዓላቸውን አከበሩ።

ከስምንት አስር ዓመታት ለላቀ ጊዜ የቆየው ትዳራቸው "ለረጅም ጊዜ አይቆይም" ተብሎ ተነግሯቸው እንደነበር ልጃቸው ገልጻለች።

እንደተባለው ግን አልሆነም። እንዲያውም ፍቅራቸው ይበልጥ ሰመረ። ረጅም ዓመታትን በትዳር ቆይተው አሁንም አብረው አሉ።

የ102 እና የ100 ዓመት የዕድሜ ባለጸጎቹ ሮን እና ጆይስ ቦንድ በሚልተን ኬይንስ ውስጥ በሚገኝ መጦሪያ መንደር ውስጥ የሚኖሩ ሲሆን በዩናይትድ ኪንግደም ረጅም ዓመት በትዳር የቆዩ እንደሆኑ ይታመናል።

ጥንዶቹ ከ81 ዓመታት በፊት በ1941 በዩናይትድ ኪንግደም ደቡባዊ ምሥራቅ ባኪንግሃምሻየር ውስጥ ነበር የተጋቡት።

ጥንዶቹ ሮን እና ጆይስ

የፎቶው ባለመብት, EXTRA CARE

ልጃቸው ኢሊን "በሠርጋቸው ጊዜ ይሄ ጋብቻ ብዙም አይዘልቅም ተብሎ ነበር። እነዚያ ሰዎች ምንኛ ተሳሳቱ?" ስትል በአግራሞት ትጠይቃለች። እውነትም ያስብላል።

ባለፈው ዓመት እነዚሁ ባለትዳሮች 80ኛ የጋብቻ ክብረ በዓላቸው ሲያከብሩ ንግሥት ኤልሳቤት "እንኳን ደስ አላችሁ!" ሲሉ በጽሁፍ መልዕክት ልከውላቸው ነበር።

ጥንዶቹ በመጀመሪያ ዕይታ በፍቅር እንደወደቁና አንዳቸው ለአንዳቸው በእኩል ደረጃ ተስማሚ እንደሆኑ ያምናሉ።

"በግንኙነታችን ውስጥ አለቃ የለም። ሁለታችንም ሰጥቶ በመቀል እናምናለን" ሲሉ ሚስትየው ጆይስ ተናግረዋል።

"ትዳራችን 81 ዓመት ይደርሳል ብለን አስበን አናውቅም። እዚህ አስገራሚ ስኬት ላይ በመድረሳችን በጣም ዕድለኞች መሆናችንን እናውቃለን። ደስ ያሰኛል" ሲሉም አክለዋል።

"አንዳንድ ጊዜ ህይወት ከባድ ይሆናል፤ ነገር ግን አብረን ልንሻገረው እንጥራልን። እርስ በርሳችንም እንጠባበቃለን" ያሉት ደግሞ ባላቸው ሮን ናቸው።

ጥንዶቹ ኢሊን እና ቢል የተባሉ ሁለት ልጆች አሏቸው። አሁን ሦስት የልጅ ልጆችን ስድስት የልጅ ልጅ ልጆች እና አንድ የልጅ ልጅ ልጅ ልጅ አይተዋል።

ጥንዶቹ እንደ አውሮፓውያኑ በ2013 ወደ ጡረታ መንደር የተዘዋወሩ ሲሆን ባል ጡረታ እስከወጡበት ጊዜ ድረስ የሼል ጋራዥ ውስጥ ሰርተዋል። ሚስት ደግሞ ደግሞ ኩዊንስዌይ በተባለ የንግድ ተቋም ይሰሩ ነበር።

ልጃቸው ወላጆቿ "ሌሎችን ማንቃት የሚችሉ አርአያ የሆኑ ጥንዶች" እንደሆኑ ተናግራለች። "ለማንም ሁል ጊዜም ሞቅ ያለ አቀባበል እና ብዙ ፍቅር ያላቸው ናቸው" ስትልም አክላለች።

"አባቴ ቤተሰቡን ለመደገፍ ጠንክሮ ይሠራ ነበር። እናቴ ደግሞ እኛን እና ቤታችንን ንጹህ ለማድረግ ትጥር ነበር። ከ81 ዓመት የትዳር ቆይታ በኋላም ቢሆን እርስ በርስ እንደሚዋደዱ እና እንደሚተሳሰቡ ለማወቅ ከእነሱ ጋር ጊዜ ማሳለፍ ብቻ ነው የሚጠበቀው" ብላለች ልጃቸው ኢሊን።