በሕንድ በሂንዱ ቤተ መቅደስ በአዲስ ዓመት በተነሳ ግርግር 12 ሰዎች ተረጋግጠው ሞቱ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሕንድ ውስጥ ሽሪ ማታ ቫይሽኖ በተሰኘው የሂንዱዎች ቅዱስ ሥፍራ ለአዲስ ዓመት አካባበር በተሰበሰቡ ሰዎች በተነሳ ግርግር አደጋ ደረሰ።
ቢያንስ 12 ሰዎች ተረጋግጠው መሞታቸውንና በርካቶች አካላዊ ጉዳት እንደደረሰባቸው ፖሊስ አስታውቋል።
ፖሊስ እንደሚለው ማታ ቫይሽኖ ቤተ መቅደስ ግርግር የተነሳው በአማኞች መካከል በተነሳ አለመግባባት ነው።
ቅዳሜ ዕለት በደረሰው አደጋ ምክንያት "እንዳዘኑ" ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ተናግረዋል።
በየዓመቱ በ10 ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በአዲስ ዓመት የመጀመሪያው ቀን ይህንን ቤተ መቅደስ ይጎበኙታል።
ቤተ መቅደሱ ሕንድ ውስጥ ከሚገኙና እጅግ ከፍተኛ ክብር ከሚሰጣቸው የእምነት ሥፍራዎች አንዱ ነው ይላል ደልሂ የሚገኘው የቢቢሲ ወኪል አንባራሳን ኤቲራጃን።
የአካባቢው ባለሥልጣናት በኮሮናቫይረስ ምክንያት በየቀኑ የሚመጡ ጎብኝዎች ቁጥር ከ25 ሺህ እንዳይበልጥ አዘዋል።
ነገር ግን ዘገባዎች እንደሚጠቁሙት ከተፈቀደው መጠን እጥፍ የሆኑ ሰዎች ካትራ በተሰኘው ከተማ አቅራቢያ በሚገኘው ቤተ መቅደስ ተገኝተው ነበር።
ቅዳሜ ጠዋት በደረሰው አደጋ በትንሹ 16 ሰዎች ጉዳት እንደደረሰባቸው መገናኛ ብዙሃን ጠቁመዋል።
በዚህ ግርግር ምክንያት የደረሰው አደጋ ተጣርቶ ቦታው ከተረጋጋ በኋላ አማኞች ዘርዘር ብለው እንዲጎበኙ እንደተፈቀደላቸው የቢቢሲ ወኪል ዘግቧል።
እስካሁን አደጋውን የሚመረምር ቡድን አልተቋቋመም።
በትዊተር ገፃቸው ሐዘናቸውን የገለፁት ጠቅላይ ሚኒስትር ሞዲ ጉዳት ለደረሰባቸው ሰዎች ቶሎ እንዲያገግሙ ያላቸውን ምኞት ገልጠዋል።
ሕንድ ውስጥ በኃይማኖታዊ በዓላት ላይ የሚደርሱ መረጋገጦች የተለመዱ ናቸው።












