ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ፖሊስ ጋዜጠኛ መዓዛ መሐመድን በችሎት እንዲያቀርብ በድጋሚ ትዕዛዝ ተሰጠው
በፌደራሉ የመጀመሪያ ፍርድ ቤት የአራዳ ሁለተኛ ልዩ ችሎት ባለፈው ሳምንት ሐሙስ ፖሊስ ጋዜጠኛ መዓዛ መሐመድን የማይፈታበትን ምክንያት ቀርቦ እንዲያስረዳ የተሰጠውን ትዕዛዝ ባለመፈጸሙ በድጋሚ ጋዜጠኛዋን ይዞ በመቅረብ በችሎት ክርክር እንዲያደርግ ታዘዘ።
ትላንት ሰኞ ታኅሣሥ 18/2014 ዓ.ም የዋለው ችሎት ፖሊስ ጋዜጠኛዋን በችሎት ይዞ በመቅረብ ያስረዳ የሚለውን ትዕዛዝ ወደ ጎን በማለት በጽሁፍ ምላሹን መላኩ የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ ያለማክበር ነው ሲልም በትዕዛዙ ላይ አስፍሯል።
ይህም ለፖሊስ እንዲገለጽ እና ዛሬ ታኅሣሥ 19 ጋዜጠኛዋን ይዞ በመቅረብ እንዲከራከር ታዟል።
ፖሊስ በጽሁፍ ለችሎቱ በሰጠው ምላሽ መዓዛ መሐመድ በቁጥጥር ስር የዋለችው በኮማንድ ፖስቱ ትዕዛዝ መሆኑን እና ተጠርጣሪዋን ይዞ በችሎት ሊያቀርብ እንደማይችል ገልጿል።
ችሎቱ በተጨማሪም የተጠርጣሪዋን ጉዳይ የያዙት መርማሪ ለምን ሳይቀርቡ እንደቀሩ በችሎት ቀርበው እንዲያስረዱም አዟል።
ጋዜጠኛ መዓዛ መሐመድ በቅርቡ በፖሊስ ከተያዙ ጋዜጠኞች መካከል አንዷ ስትሆን ከሁለት ሳምንት በፊት ታኅሣሥ 02/2014 ዓ.ም ከአባቷ ቤት ሲቪል በለበሱ የፀጥታ ኃይሎች ነበር በቁጥጥር ስር የዋለችው።
በተጨማሪም ከሳምንታት በፊት በቁጥጥር ስር ከዋሉት በርካታ የሚዲያ ሠራተኞች መካከል የተራራ ኔትወርክ መስራች እና ዋና አዘጋጅ ታምራት ነገራ ብቻ በኦሮሚያ ክልል ገላን ከተማ በሚገኝ ችሎት ታኅሣሥ 07/2014 ዓ. ም. ቀርቧል።
በወቅቱም ፖሊስ በታምራት ላይ የጠየቀው 14 ተጨማሪ የምርመራ ቀናት ተፈቅዶ ጋዜጠኛውም በእስር ላይ ይገኛል።
እያስፔድ ተስፋዬ፣ አሚር አማን ኪያሮ፣ ቶማስ እንግዳ፣ አዲሱ ሙሉነህና ሌሎች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተከትሎ በቁጥጥር ስር የዋሉ ሌሎች የሚዲያ ሠራተኞች ሲሆኑ ከቤተሰቦቻቸው የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው እስካሁን ድረስ ፍርድ ቤት አልቀረቡም።
የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ከሥራቸው ጋር በተያያዘ በእስር ላይ የሚገኙ ሁሉንም ጋዜጠኞች በአስቸኳይ እና ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መፍታት አለባቸው ሲል ለጋዜጠኞች መብት የሚቆረቆረው ሲፒጄ በቅርቡ ጠይቋል።
ኢትዮጵያ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በመጠቀም የፕሬስ አባላትን ከማሰር መቆጠብ አለባት ሲል ሲፒጄ ከሰሞኑ ባወጣው መግለጫ መጠየቁ ይታወሳል።
ኢትዮጵያ ከእርስ በርስ ጦርነቱ ጋር በተያያዘ የአስቸኳይ ጊዜ ካወጀችበት ጥቅምት 23/2014 ዓ.ም ጀምሮ 14 ጋዜጠኞችን ማሰሯን ሲፒጄ አስፍሯል።
በእስር ላይ ከዋሉት መካከል መንግሥታዊው የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢቢሲ) የትግርኛ ቋንቋ የሬድዮ አገልግሎት የቀድሞ ሁለት ጋዜጠኞች፣ የዩቲዩብ ቻናል የሆነው ኡቡንቱ ቴሌቪዥን ዋና አዘጋጅ፣ የተራራ ኔትወርክ ዋና አዘጋጅ እንዲሁም የሮሃ ቴሌቪዥን ተባባሪ መስራች ይገኙበታል።
ከዚህም በተጨማሪ የአሶሺየትድ ፕሬስ የቪዲዮ ጋዜጠኛ፣ የካሜራ ባለሙያ እና የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ጋዜጠኛ ከኦሮሞ ነፃነት ጦር ታጣቂዎች ዘገባ ጋር በተያያዘ በእስር ላይ ውለዋል።