"ቤተ-እስራኤላዊያንን ማግኘቴን በጥቁር አይሁዳዊነቴ እንድኮራ አድርጎኛል"

ናዲን እየሩሳሌም ውስጥ
የምስሉ መግለጫ, ናዲን እየሩሳሌም ውስጥ
ታትሟል

ጥቁር በመሆኗ ብቻ ለዘመናት አይሁዳዊነቷ ጥርጣሬ ውስጥ የገባው ናዲን ባችለር-ሃንት ወደ እስራኤል አቅንታ ጥቁር አይሁዳዊ ኢትዮጵያዊያን ስታገኝ አንዳች ነገር ነው የተሰማት። ታሪኳን እንዲህ ትተርካለች።

Short presentational grey line

ጥቁር አይሁዳዊ ሆኖ ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ መኖር ቀላል ነገር አይደለም። ስለዚህ እንደእኔ ዓይነት ሰው ወደ አይሁዳዊያን ሲቀላቀል ጎልቶ ይወጣል።

ለጥቁር ሰዎች አይሁዳዊ ነኝ ብዬ ስነግራቸው ይገርማቸዋል። ያለም አይመስላቸውም። እርግጥ ነው ጎልቶ መውጣቱ ለየት ያለ ስሜት ይሰጣል። በሌላ በኩል ግን ጥቁር አይሁዳዊ መሆን ያልተፈቀደ የሚመስል ዓይነት ስሜት አለው።

እኔ ግማሽ ጃማይካዊ ግማሽ እንግሊዛዊ ነኝ። ምንም እንኳ በጃማይካውው አባቴ በኩል የአይሁድ ዘር ቢኖርብኝም ሐይማኖቱን የመረጥኩት ካደግኩ በኋላ ነው።

ያደግኩት በርሚንግሃም በተሰኘችው ከተማ ይን ያህል ሐይማኖተኛ በማይባል ቤተሰብ ውስጥ ነው። ካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ ገብቼ አይሁዳዊያንን ስተዋወቅ ግን ወደ ማንነቴ መመለስ ጀመርኩ። ከዚያም እምነቴን ቀይሬ አይሁድ ሆንኩ። ነገር ግን የሚደርስብኝ ዘረኝነት፣ መገለልና የፀረ-ሴማዊነት ጥቃት ቀላል አልነበረም። ቢሆንም በመረጥኩት መንገድ እጅግ ደስተኛ ነኝ።

'ብላክ ላይቭስ ማተርስ' የተሰኘው እንቅስቃሴ በተጋጋለበት ወቅ ስለ ዘረኝነት ብዙ መባል ተጀመረ። ይህ ጉዳይ ነው ወደ አይሁድ መገኛ እስራኤል እንድጓዝ በዓለማችን ትልቁን የጥቁር አይሁዳዊያንን መንደር እንድጎበኝ ያደረገኝ።

ከኢትዮጵያ የመጡት ጥቁር አይሁዳዊያን [ቤተ-እስራኤላዊያን] ጥቁርነትና አይሁዳዊነት ተምታቶባቸው አያውቅም። ለዚህም ነው ለእኔም መንገዴን ያጠሩልኛል ብዬ ያሰብኩት።

line

እስራኤል ያሉት ኢትዮጵያዊያን አይሁዶች ማን ናቸው?

  • ቤተ እስራኤላዊያን በመባል የሚታወቁት እኒህ ሕዝቦች በጣም ጥንታዊ የሆነና ለየት ያለ የአይሁድ እምነት ተከታዮች ናቸው፤
  • በ1980ዎቹ እና 90ዎቹ [በፈረንጆቹ] በምስጢር በተካሄዱ ዘመቻዎች 28 ሺህ ገደማ ኢትዮጵያዊያን አይሁዶች ወደ እስራኤል መጥተዋል፤
  • በሺዎች የሚቆጠሩት ሱዳን ወደሚገኙ ካምፖች ለመድረስ በእግር ተጉዘዋል። ከ1500 በላይ ሰዎች በዚህ ጉዞ እንደወጡ ቀርተዋል፤
  • ከ2015 ጀምሮ ደግሞ እስራኤል ያሉት አይሁዳዊያን ዘመድ አዝማድ የሆኑ 4500 ቤተ እስራኤላዊያን ወደ እስራኤል መጥተዋል።
line
ቤተ አስራኤላውያን ከ30 ዓመት በፊት ከኢትዮጵያ ወደ አስራኤል በገቡበት ጊዜ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ቤተ አስራኤላውያን ከ30 ዓመት በፊት ከኢትዮጵያ ወደ አስራኤል በገቡበት ጊዜ

በምስጢራዊ መንገድ ወደ እስራኤል ከመምጣታቸው በፊት ኢትዮጵያዊያን አይሁዶች ሁሉም አይሁዳዊ ጥቁር ነበር የሚመስላቸው።

በሦስት ዓመቷ ወደ እስራኤል የመጣችው ፐኒና አገኘሁ "እየሩሳሌም ስንደርስ ምን ሊሆን እንደሚችል እናልም ነበር" ስትል ነግራኛለች። "ቅድስቲቱ ምድር፤ ወተትና ማር የሚዘንብባት፤ ወርቅ የሚፈስባት፤ ሁሉም ጥቁርና አይደሁዳዊ የሆነባት ይመስለን ነበር።"

ለኢትዮጵያዊያን አይሁዳዊያን ጥቁር ባልሆነ ማኅበረሰብ ሕይወትን መግፋት በጣም አስቸጋሪ ነበር። ማኅበረሰቡ በጥቁር አገር አናሳ የአይሁድ ማኅበረሰብ ከመሆን በአይሁድ አገር ውስጥ አናሳ ጥቁር ወደ መሆን ተሸጋገረ።

ምንም እንኳ እኔ ጥቁር አይሁዳዊ መሆኔን ለሌሎች ለማሳመን የማደርገው ጥረት ባይገባቸውም፣ የመገንጠል ስሜቱና አይሁድ መሆንን ለማሳመን የሚደረገው ድርጊት ግን ያመሳስለናል።

አሁን በግምት 155 ሺህ ቤተ እስራኤላዊያን እስራኤል ውስጥ ይገኛሉ። ይህም ከአገሪቱ ጠቅላላ ሕዝብ ከ2 በመቶ በታች ነው።

"አናሳ መሆንሽ ሲገባሽ ነገሮች ከባድ ይሆናሉ" ትላለች ፕኒና። "ሁሌም ለጓደኞቼና ለሥራ አጋሮቼ የምላቸው ከአናሳ ማኅበረሰብ መጥቶ አናሳ መሆን ምን እንደሚመስል አይገባችሁም ነው።"

የራድዮ ዘጋቢ ፕሮግራም ሰሠራ ነው በርካታ ነገሮችን ማስተዋል የጀመርኩት። በአንድ በኩል በርካታ ጥቁር አይሁዶችን አግኝቶ ታሪካቸውን መስማት ያስደስታል። ነገር ግን እኔ የምከተለው 'የአሽኬናዚ' አሊያም ምሥራቅ አውሮፓዊ አመጣጥ ያለው የአይሁድ እምነትና ባሕል ከቤተ እስራኤላዊያኑ ይለያል።

ከቤተ እስራኤላዊያን ጋር እየሩሳሌም ውስጥ ያከበርኩት የስግድ ፌስቲቫል ለምሳሌ በጣም ለየት ያለና ለእኔ አዲስ የሆነብኝ ነገር ነው። እኔ የምፀልየው በእብራይስጥ ቋንቋ ነው፤ እነሱ ደግሞ ጥንታዊ የኢትዮጵያ ቋንቋ በሆነው ግዕዝ ነው።

የቤተ እስራኤላዊያን ሐይማኖታዊ አባቶች [ቀሲም] ስግድ በተሰኘው ወደ እየሩሳሌም መመለስን በሚዘክረው በዓል ቀን ፀሎት ያደርሳሉ።

ብዙዎች ይህ በዓል እስራኤል ውስጥ ተቀባይነት አግኝቶ ትልቅ ይሆናል የሚል ተስፋ አላቸው።

ነገር ግን ቤተ እስራኤላዊያን ልክ እንደ ዩናይትድ ኪንግደም ሁሉ እስራኤል ውስጥ መገለል እንደሚደርስባቸው፤ ፖሊስ እንደሚጨክንባቸውና ዘረኝነት እንደሚገጥማቸው አጫውተውኛል።

ፕኒና አገኘሁ እና ናዲን ባችለር ሐንት
የምስሉ መግለጫ, ፕኒና አገኘሁ እና ናዲን ባችለር ሐንት

ምንም እንኳ ኢትዮጵያዊያን አይደሁዶች በብዙ የሕይወት መንገድ ልቀው ቢገኙም አናሳ እንደመሆናቸው ስቃይ ደርሶባቸዋል።

በ2019 ሰሎሞን ተካ የተባለ ያልታጠቀ ኢትዮጵያዊ በፖሊስ መገደሉን ተከትሎ ከባድ ተቃውሞ ነበር። የፖሊስ መኮንኑ በአሁኑ ወቅት ፍርዱን እየተከታተለ ይገኛል።

ቤተ እስራኤላዊያን ቤት ከሚያከራዩ ሰዎችም መድልዎ ይደርስባቸዋል። አልፎም በ1990ዎቹ መንግሥት ከቤተ እስራኤላዊያን የተለገሰ ደም በድብቅ ሲያስወግድ ነበር።

"ይመስለኛል በዚያን ወቅት ነው ቤተ እስራኤላዊያን የእስራኤል ማኅበረሰብ እኩል አድርገው እንደማያዩን የተረዳነው" ትላለች ኢትዮጵያዊት አይሁዷ ጠበቃና የመብት ተሟጋች ሮኒ ማልካይ።

"ነገር ግን ጥረታችንን እንቀጥላለን። ምክንያቱም እስራኤል መኖር ስለምንፈልግ። ማንም በተለየ መንገድ ሊያየን አይገባም" ስትል ነግራኛለች።

እስራኤል ውስጥ በነጭና በጥቁር አይሁዶች መካከል ያለውን ልዩነት ለማጥበብ ብዙ ከጣሩት መካከል አንድ ዳኒ ሊሞር ነው።

የቀድሞው የሞሳድ አዛዥ የነበረው ሊሞር ቤተ እስራኤላዊያንን ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ እስራኤል እንደሚጡ ደረገውን ምስጢራዊ ዘመቻ [ኦፕሬሽን] መርቷል።

ሊሞርና ባለቤቱ የሳባዝ እራት አብሬ እንድቋደሳቸው ጠርተውኝ ቤታቸው በተገኘሁበት ከናይጄሪያ ኢግቦ ማኅበረሰብ የመጣችውን ጥቁር አይሁዳዊት ኦራ ዮቻናን ተዋወቅኩ።

"እርስ በርስ ተቻችለን መኖር እንዴት እንደምንችል መማር አለብን" አለ ዳኒ። "የአይሁዳዊያን ታሪክ በበርካታ የመገፋት፣ የግድያ፣ ያልፈቃድ እምነት፣ ባሕል፣ አለባበስ፣ ቋንቋ የመቀየር ታሪክ የተሞላ ነው። አይሁዳዊ ማንነት ማለት በውጫዊ ገጽታ አሊያም በቋንቋ ወይም በምንበላው ምግብ የሚለካ ሳይሆን በጋር እምነትና አስተሳሰብ የሚመዘን ነው።"

ምንም እንኳ ጥቁር መሆን አይሁዳዊ መሆንን ባይቀንሰውም ከጥቁር አይሁዳዊያን ጋር የነበረኝ ቆይታ የአይሁድ ታሪክ የጥቁር ታሪክ አካል እንደሆነ፤ የጥቁር ታሪክ ደግሞ የአይሁድ ታሪክ አካል እንደሆነ እንድረዳ አድርጎኛል።