አሜሪካ እና ሩሲያ በዩክሬን ድንበር ስለሰፈሩ የሩሲያ ወታደሮች ለመነጋገር ተስማሙ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጄኔቫ ውስጥ ለመወያየት ተስፋ እንደሚያደርጉ ከገለጹ በኋላ በዩክሬን ድንበር አካባቢ ስለሰፈሩት ወታደሮቻቸው በመጪው ወር ንግግሮች ሊጀመሩ እንደሚችሉ የአሜሪካ ባለሥልጣናት አስታውቀዋል።
የሩሲያው መሪ አሁን ያለውን ፍጥጫ ለማርገብ የኔቶን የወደፊት እጣ ፈንታ በተመለከተ ማረጋገጫዎችን እንደሚፈልጉ ገልጸዋል።
"አሁን ኳሷ ያለችው በእነሱ ሜዳ ውስጥ ነው፤ የሆነ ነገር በምላሹ ሊሰጡን ይገባል" ሲሉ ተደምጠዋል ፑቲን በዓመታዊው ጋዜጣዊ መግለጫቸው ላይ።
ፕሬዝዳንቱ አክለውም አስፈላጊ ከሆነ ወታደራዊ እርምጃ እንደሚወስዱ፣ ነገር ግን ዩክሬንን የመውረር እቅድ እንደሌላቸው አስረግጠዋል።
የዩክሬን የደኅንነት ባለሥልጣናት ግን ከ100 ሺህ በላይ የሚሆኑ የሩሲያ ወታደሮች በድንበሯ በኩል በጣም ተጠግተው እንደሚገኙ የገለጸች ሲሆን፣ አሜሪካ ደግሞ ዩክሬን ማንኛውም አይነት ጥቃት የሚፈጸም ከሆነ ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ አይነት ማዕቀቦችን እንደምትጥል አስጠንቅቃለች።
ከፍተኛ የዋይት ሐውስ ባለሥልጣናት በበኩላቸው ሩሲያ ኔቶ ሁሉንም ወታደራዊ መስፋፋቶቹን እንዲያቆም እንዲሁም ዩክሬን ከኔቶ አባልነት እንድትወጣ መጠየቋን በተመለከተ ምንም አይነት ምላሽ ከመስጠት ተቆጥበዋል።
"እናንተ ናችሁ ማስተማመኛ ልትሰጡን የሚገባው፤ አሁንና በፍጥነት እንድታረጋግጡልን እንፈልጋለን" ብለዋል። ፕሬዝደንት ፑቲን አክለውም ወታደራዊ እርምጃን የማይመርጡት እንደሆነም ገልጸዋል።
የዋይት ሐውስ ፕሬስ ሴክሬታሪ ጄን ሳኪ በበኩላቸው ምንም እንኳን በዲፕሎማሲያዊ ንግግሮች የመጨረሻ ስምምነት ላይ ለመድረስ ባይቻልም አሜሪካ ግን ይህንን ለማሳካት እንደምትጥር አስታውቀዋል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ባለሥልጣን የሆኑት ሊዝ ቴስ ደግሞ ሞስኮ በሚቀጥለው ወር ንግግር ለማድረግ ፈቃደኛነቷን መግለጿን በጥሩ ጎኑ እንደሚመለከቱት በመግለጽ፣ ሩሲያ ዩክሬን ላይ ወታደራዊ እርምጃ የምትወስድ ከሆነ ግን የአገሪቱን ኢኮኖሚ የሚያሽመደምድ ማዕቀብ እንደሚጠብቃት አሳስበዋል።
በቅርብ ሳምንታት በሩሲያ እና በዩክሬን መካከል የተፈጠረው ወታደራዊ ፍጥጫ እንዳለ ሆኖ በአገሪቱ ምሥራቃዊ ክፍል ግን ተስፋ ሰጪ ነገር ተስተውሎ ነበር።
በሩሲያ የሚደገፉት የዩክሬን ተገንጣይ ቡድኖች ላላፉት ሰባት ዓመታት ከዩክሬን ጋር ሲያደርጉት የነበረውን ጦርነት ለማቆምና የተኩስ አቁም ስምምነት ለማድረግ ተስማምተዋል።
ፈረንሳይ እና ጀርመን የተኩስ አቁም ስምምነቱ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ እንዲሆንና የእስረኞች ለውውጥ እንዲደረግም ጠይቀዋል።












