ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በተደረጉ የእግር ኳስ ጨዋታዎች እነማን አሸነፉ?

ማንችስተር ሲቲ ግብ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

በአውሮፓ አዲሱ የኮሮናቫይረስ ዝርያ ኦሚክሮን በስፋት መሰራጨት መጀመሩን ተከትሎ በርካታ የእግር ኳስ ጨዋታዎች እየተስተጓጎሉ ነው፤ ነገር ግን ባሳለፍነው ቅዳሜና እሁድ በእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ፣ በጣልያን ሴሪ እንዲሁም በስፔናን ላሊ ጋ በርካታ ጨዋታዎች ተካሂደዋል።

በእንግሊዝ ፕሪምየር ምንም እንኳን ጥቂት የማይባሉ ወሳኝ ጨዋታዎች በኦሚክሮን ስርጭት ምክንያት ለሌላ ጊዜ ቢተላለፉም በሊጉ ከአንድ እስከ ሦስት የሚገኙት ቡድኖች ግን ጨዋታቸውን አድርገዋል።

ማንቸስተር ሲቲ ኒውካስልን አራት ለዜሮ በሆነ ውጤት በማሸነፍ መሪነቱን ያረጋገጠ ሲሆን ቼልሲዎች ደግሞ ከዎልቭስ ያደረጉትን ጨዋታ ያለምንም ግብ አቻ ጨርሰዋል። ቼልሲዎች በአራት ጨዋታ ለሦስተኛ ጊዜ ነው አቻ የወጡት።

ትናንት ምሽት ደግሞ ሊቨርፑል በአዲሱ አሰልጣኝ አንቶኒዮ ኮንቴ የሚመሩት ቶተንሀሞችን ገጥሟል። ጨዋታው ምንም እንኳን በሙከራዎችና በግቦች የታጀበ ቢሆንም ውጤቱ ግን አቻ ነበር። ጨዋታውም 2 ለ 2 ተጠናቋል።

ይህንን ተከትሎ ማንቸስተር ሲቲዎች በ18 ጨዋታዎች ሊጉን በ44 ነጥብ መምራት የጀመሩ ሲሆን ሊቨርፑል ደግሞ በ41 ነጥብ የሁለተኛውን ቦታ ይዟል።

ቼልሲ በ38 ነጥብ ሦስተኝነቱን አሁንም ማስጠበቅ ያለ ሲሆን አርሰናል፣ ዌስት ሀም፣ ማንቸስተር ዩናይትድ እና ቶተንሀም ለአራተኛው ቦታ እየተፎካከሩ ይገኛሉ።

በርንሌይ ኒውካስል እና ኖርዊች ሲቲተ ደግሞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ የሚገኙ ቡድኖች ናቸው።

ማን ሲቲ

የፎቶው ባለመብት, Lynne Cameron - Manchester City

በጣልያን ሴሪ አ የሊጉ መሪ ኢንተር ሚላን ከሳሌኒታና ያደረገውን ጨዋታ 5 ለባዶ በሆነ ውጤት በማሸነፍ በ48 ነጥብ መሪነቱን ማረጋገጥ ችሏል። በጉጉት የተጠበቀው የናፖሊ እና የሚላን ጨዋታ ደግሞ በናፖሊ አንድ ለባዶ አሸናፊነት ተጠናቋል።

ይህን ተከትሎ ናፖሊ በ39 ነጥብ ከኢንተር ሚላን በመቀጠል ሁለተኝነቱን ያረጋገጠ ሲሆን ኤሲ ሚላኖች ደግሞ ምንም እንኳን ቢሸነፉም በተመሳሳይ 39 ነጥብ በግብ ክፍያ ተበልጠው ሦስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።

የውጤት ቀውስ ውስጥ የሚገኙት ጁቬንቱሶች ደግሞ ቅዳሜ ዕለት ቦሎኛን ሁለት ለምንም በማሸነፍ በ25 ነጥብ 7ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።

በስፔን ላሊጋ ቅዳሜ ዕለት የቀድሞ ተጫዋቻቸውን በአሰልጣኝነት የቀጠሩት ባርሴሎናዎች ከኤልቼ ያደረጉትን ጨዋታ 3 ለ 2 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችለዋል።

ከቻምፒየንስ ሊግ የምድብ ጨዋታ ማለፍ ያቃታቸው ባርሴሎናዎች በሊጉም ቢሆን ወደ ቀድሞ ቦታቸው ለመመለስ ብዙ ይቀራቸዋል። በአሁኑ ሰዓት በ28 ነጥብ 7ኛ ደረጃ ላይ ነው የሚገኙት።

ያለፈው ዓመት የላሊጋው አሸናፊ አትሌቲኮ ማድሪድ ደግሞ በሲቪያ ሁለት ለአንድ መሸነፉን ተከትሎ በ29 ነጥብ አምስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። ሲቪያ ደግሞ አንድ ቀሪ ጨዋታ እየቀረው በ37 ነጥብ ሁለተኛ ነው።

የሊጉ መሪ ሪያል ማድሪድ ትናንት ምሽት የነጥብ ልዩነቱን ማስፋት የሚችልበትን ዕድል ሳይጠቀም ቀርቷል። እሁድ ምሽት ከካዲዝ የተገናኙት ሪያል ማድሪዶች ጨዋታውን ያለምንም ግብ ዜሮ ለዜሮ በሆነ አቻ ውጤት አጠናቀዋል።