ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ከጦር ግንባር መመለሳቸውን ገለጹ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የአገሪቱ ሠራዊት ከህወሓት ኃይሎች ጋር የሚያደርገውን ውጊያ ለመምራት በጦር ሜዳ የነበራቸውን ቆይታ አጠናቀው ወደ አዲስ አበባ መመለሳቸውን ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ጦር ግንባር አምርተው ለሁለት ሳምንታት የቆዩ ሲሆን ዛሬ ኅዳር 29/2014 ዓ.ም ባወጡት መግለጫ የግንባር ጉዟቸው የመጀመሪያ ምዕራፍ መጠናቀቁን ገልጸው ለተወሰኑ ጊዜያት ወደ ቢሯቸው እንደተመለሱ አመልክተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል እየተካሄደ ያለውን ጦርነት በአካል ተገኝተው ለመምራት መወሰናቸውን ያሳወቁት ከሁለት ሳምንታት በፊት ኅዳር 13/2014 ዓ.ም ነበር።
በወቅቱ ይፋ እንዳደረጉት "ጊዜው አገርን በመሥዋዕትነት መምራት የሚያስፈልግበት ነው" በማለት እራሳቸው የአገሪቱ ሠራዊት በተሰለፈበት ግንባር በመገኘት ለመምራት ከማክሰኞ ኅዳር 14/2014 ዓ.ም ጅምሮ ወደ ጦር ሜዳ እንደሚያመሩ ማሳወቃቸውን ተከትሎ ነበር ወደዚያው ማቅናታቸው የተነገረው።
አንድ ዓመት ያስቆጠረው ጦርነት ተባብሶ በአማራና በአፋር ክሎች ውስጥ በቀጠለበትና የህወሓት ኃይሎች በርካታ ቦታዎችን ተቆጣጥረው ሰሜን ሸዋ መግባታቸው ከተነገረ በኋላ ነበር ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጦር ግንባር በመገኘት ሠራዊቱን ለመምራት የወሰኑት።
የኢትዮጵያ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ የሆኑት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከአዲስ አበባ ወጥተው ሠራዊታቸውን ለመምራት ወደ ጦር ሜዳ በሄዱበት ወቅት የመንግሥት የዕለት ከዕለት ሥራ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ደመቀ መኮንን እንደሚከናወን ተገልጾ ነበር።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በተለያዩ የጦር ግንባሮች በቆዩባቸው ሁለት ሳምንታት ውስጥ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊትና የክልል ኃይሎች ባካሄዱት ዘመቻ ቁልፍ የሚባሉ እና በርካታ የአፋርና የአማራ አካባቢዎች መለቀቃቸው ይታወሳል።
ከጦር ግንባር ወደ መደበኛ ሥራቸው መመለሳቸውን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ "ዛሬም ሆነ ወደፊት ጠላቶቻችን ጉልበታቸው ዝሎ፣ የጥላቻና የጠበኝነትን መንገድ ጥለው፣ የፍቅርና የሰላምን መንገድ እስኪመርጡ ትግላችን ይቀጥላል" ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ መደበኛ ሥራቸው መመለሳቸውን ይግለጹ እንጂ "ትግሉ ገና አልተጠናቀቀም። ነጻ ያልወጡ አካባቢዎች አሉን" በማለት አገሪቱ የገጠማት ፈተና ዳግመኛ እንዳይመጣ ዘላቂ መፍትሔ ሊሰጠው ይገባል ሲሉ ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ጦር ግንባር ለመሄድ መወሰናቸውን ባሳወቁበት ጊዜ ሌሎችም ዜጎች እንዲከተሏቸው "ታሪክ ከሚያደንቃቸው የኢትዮጵያ ልጆች አንዱ ለመሆን የምታስቡ ሁሉ ለሀገራችሁ ስትሉ ዛሬውኑ ተነሡ፤ ግንባር ላይ እንገናኝ" በማለት ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን በርካታ ታወቂ ሰዎች በዘመቻው ለመሳተፍ ፈቃደኝነታቸውን መግለጻቸው ይታወሳል።
ባለፉት ሁለት ሳምንታት በአማጺው ኃይል ቁጥጥር ስር የነበሩ በርካታ የአፋርና የአማራ ክልል አካባቢዎች በኢትዮጵያ መንግሥት ኃይሎች ቁጥጥር ስር ተመልሰው የገቡ ሲሆን፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩም በተለያዩ ግንባሮች ከሠራዊቱ እንደነበሩ የአገር ውስጥ ቴሌቪዥኖች አሳይተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ቢሯቸው መመለሳቸውን በገለጹበት መግለጫ ላይ "ያቀረብኩትን ጥሪ ተቀብላችሁ ሕይወታችሁን፣ ጉልበታችሁን፣ ሀብታችሁን፣ ዕውቀታችሁን፣ ጊዜያችሁንና ሙያችሁን ለሠጣችሁ ሁሉ በኢትዮጵያ ስም ላመሰግናችሁ እወዳለሁ" ብለዋል።
ጨምረውም የመጀመሪያውን ምዕራፍ፣ "ዘመቻ ለኅብረ ብሔራዊ አንድነትን" በሁለት ሳምንት ውስጥ መሳካቱን አመልክተው፣ የመከላከያ ሠራዊት፣ የየክልሎቹ ልዩ ኃይሎች፣ የፌዴራል ፖሊስ አባላት እና ሚሊሻዎችና ታጣቂዎች "በከፈላችሁት መሥዋዕትነት ለልጆቻችን የምንነግረው ድንቅ ታሪክ ሠርታችኋል" በማለት አድናቆታቸውን ገልጸዋል።
ትግራይ ክልል ውስጥ ተጀምሮ ወደ አፋርና አማራ ክልሎች ተስፋፋው ጦርነት አንድ ዓመት ያለፈው ሲሆን በርካታ ሰብአዊና ቁሳዊ ጉዳት ማስከተሉ ይታወቃል።
በጦርነቱ ሳቢያ በሚሊዮኖች ሚቆጠሩ ሰዎች ለእርዳታ ጠባቂነት የተጋለጡ ሲሆን በመቶ ሺዎች ደግሞ ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተቋማት አሳውቀዋል።