በግድያ የተከሰሱት የሚሽገን ትምህርት ቤት ጥቃት አድራሽ ወላጆች ተያዙ

ልጃቸው የተኩስ ጥቃቱን ከማድረሱ በፊት ይታዩበት የነበሩ ምልክቶችን ችላ በማለት የተከሰሱት ጄምስ እና ጄኒፈር ክሩምብሌይ

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ, ልጃቸው የተኩስ ጥቃቱን ከማድረሱ በፊት ይታዩበት የነበሩ ምልክቶችን ችላ በማለት የተከሰሱት ጄምስ እና ጄኒፈር ክሩምብሌይ
ታትሟል

የአሜሪካ ዐቃቤ ሕግ በሚሽገን ትምህርት ቤት ውስጥ ሰዎችን በመግደል የተጠረጠረው ግለሰብ ወላጆችን በቸልተኝነት ሰው በመግደል ወንጀል ክስ መስርቶባቸዋል።

ልጃቸው ጥቃቱን ከማድረሱ በፊት ይታዩበት የነበሩ ምልክቶችን ችላ በማለት የተከሰሱት ጄምስ እና ጄኒፈር ክሩምብሌይ የእስር ማዘዣ ወጥቶባቸው የነበረ ሲሆን፤ በዲትሮይት ግዛት ውስጥ በቁጥጥር ስር ውለዋል።

የ15 ዓመት ልጃቸው ኤታን ክሩምብሌይ በዚህ ሳምንት ከዲትሮይት በስተሰሜን 35 ማይል ርቀት ላይ በምትገኘው ኦክስፎርድ የአባቱን ሽጉጥ ተጠቅሞ የክፍል ጓደኞቹ ላይ ተኩሷል የሚል ክስ ቀርቦበታል።

ሆኖም ሽብርተኝነትን ጨምሮ የቀረቡበትን ክሶች ጥፋተኛ አይደለሁም ሲል አስተባብሏል።

ጄምስ እና ጄኒፈር ክሩምብሊ እያንዳንዳቸው አራት ደረጃ ያለው ክሶች ይጠብቃቸዋል።

የኦክላንድ አውራጃ ባለሥልጣናት ጠበቆቻቸው ተከሳሾቹን በስልክ ሊያገኟቸው ባለመቻላቸው ጥንዶቹን እየፈለጉ ነበር።

በርካታ መርማሪዎች፣ የኤፍቢአይ እና የአሜሪካ የፀጥታ አካላት የጥቃት ፈጻሚውን ወላጆች ሲፈለጉ ነበር።

ጠበቆቻቸው ሻነን ስሚዝ እና ማሪል ሌማን ወላጆቹ "ከሕግ አስከባሪ አካላት እየሸሹ አይደለም። ለደኅንነታቸው ሲሉ ተኩሱ በነበረበት ምሽት ከተማውን ለቀው ወጥተዋል" ሲሉ ለቢቢሲ በላኩት የጽሑፍ መልዕክት አስታውቀዋል።

ጠበቆቹ አክለውም ጥንዶቹ ፍርድ ቤት ለጉዳዩ ይመለሳሉ ያሉ ሲሆን፤ ይህም ከአርብ በኋላ ይከናወናል ተብሎ ይጠበቃል።

ማክሰኞ በተፈፀመው ጥቃት አራት ልጆች ሲሞቱ ሰባት ደግሞ ቆስለዋል። ሟቾቹም ከ14 እስከ 17 ዓመት የሚሆኑ ልጆች ናቸው።

ማክሰኞ በተከፈተው ጥቃት አራት ልጆች ሲሞቱ ሰባቱ ደግሞ ቆስለዋል። ሟቾቹም ከ14 እስከ 17 ዓመት የሚሆኑ ልጆች ናቸው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ማክሰኞ በተከፈተው ጥቃት አራት ልጆች ሲሞቱ ሰባቱ ደግሞ ቆስለዋል። ሟቾቹም ከ14 እስከ 17 ዓመት የሚሆኑ ልጆች ናቸው።

የጥቃት አድራሹ ወላጆች ለምን ተከሰሱ?

አርብ ዕለት የኦክላንድ አውራጃ ዋና ዐቃቤ ሕግ ካረን ማክዶናልድ በልጅ ወንጀል ወላጆችን መክሰስ እጅግ ያልተለመደ መሆኑን አምነዋል።

የእሳቸው ቢሮ ባደረገው ምርመራ፣ ባለፈው አርብ አባት ጥቃቱን ካደረሰው ልጁ ጋር ሆኖ በጥቃቱ ጥቅም ላይ ውሏል የተባለውን መሣሪያ ሲገዛ ነበር።

በዕለቱ በልጁ የማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የሰፈው ጽሑፍ የአባቱን አዲስ መሣሪያ "አዲሷ የኔ ቆንጆ" ሲል ከልብ ምስል (ኢሞጂ) ጋር አድርጎ አጋርቷል።

ልጃቸው ጥቃቱን ከማድረሱ አንድ ቀን አስቀድሞ አንዲት መምህር ይህ ተማሪ ከኢንተርኔት ላይ ጥይቶችን ሲፈልግ እንዳየችው ተናግራለች።

በዚህም ምክንያት ከትምህርት ቤቱ አስተዳደር ጋር ስብሰባ መደረጉን ዋና ዋና ዐቃቤ ሕጓ ተናግረዋል። ከዚያም ለእናቱ ክሩምብሊ ስለሁኔታው ቢነገራትም "አልተናደድኩብህም። እንዳትያዝ መማር አለብህ" በማለት ለልጇ መልዕክት ልካለች።

እናም ማክሰኞ ማለዳ ላይ ጥቃቱ ከመፈጸመሙ ከሰዓታት በፊት መምህራኖች በልጁ የተጻፈ ማስታወሻ ማግኘታቸውን ተከትሎ ወላጆቹን ወደ ትምህርት ቤት ጠርተው አነጋግረዋል።

ልጁ ላይ የተገኙት በርካታ የጠመንጃ እና በደም የተጨማለቁ ሰዎች ሥዕሎች፤ "ሐሳቦች አይቆሙም። እርዳኝ" ከሚል ጽሑፍ ጋር እንዲሁም "ደም በሁሉም ቦታ "፣ "ሕይወቴ ከንቱ ናት" እና "ዓለም ሞታለች" የሚሉ እንደነበር ዐቃቤ ሕግ ገልጿል።

የትምህርት ቤት ኃላፊዎች ጥንዶቹ ልጃቸውን ወደ ሥነ ልቦና አማካሪ እንዲወስዱ ሐሳብ ሰጥተዋቸው ነበር።

ወላጆቹ ልጃቸው በዚያ ቀን ትምህርት ቤት እንዲሄድ አልፈለጉም ነበር ያሉት ዐቃቤ ሕጓ ማክዶናልድ፤ ሽጉጡን እንደያዘው ወይም እንዳልያዘው እንዳልጠየቁት ወይም ትምህርት ቤት ይዞት የሄደው ቦርሳ ውስጥ እንዳልፈለጉት አክለዋል።

ጥቃቱ በተፈጸመ ቀን እናቱ "ኤታን፣ እንዳታደርገው" በማለት የጽሑፍ መልዕክት ለልጃቸው የላኩ ሲሆን፤ ከደቂቃዎች በኋላ ባለቤቷ ደግሞ ለፖሊስ ደውሎ ሽጉጡ መጥፋቱን እንደሳወቀ ዐቃቤ ሕጓ ተናግረዋል።

ነገር ግን ልጁ ቀድም ብሎ ከትምህርት ቤቱ መታጠቢያ ቤት ወጥቶ በተማሪዎቹ ላይ ተኩስ ከፍቶ ነበር።

ዋና ዐቃቤ ሕጓ ማክዶናልድ ክሱ እናቱን ተጠያቂ ለማድረግ እና የጠመንጃ ባለቤትነትን በተመለከተ መልዕክት ለማስተላለፍ ያለመ ነው ብለዋል።

ዐቃቤ ሕጓ ከዚህ ቀደም ሽጉጡ በሕጋዊ መንገድ የተገዛ ቢሆንም ልጁ እንዲጠቀምበት "ነጻ በሆነ መንገድ የቀረበ ይመስላል" ብለዋል።

እንደ እሳቸው ገለጻ፤ ተጠርጣሪው ሽጉጡን በወላጆቹ መኝታ ክፍል ውስጥ ካለ ያልተቆለፈ መሳቢያ ወስዶ ወደ ትምህርት ቤት አምርቷል።

የአሜሪካ የፌደራልም ሆነ የግዛቶች ሕግ የጦር መሣሪያ ባለቤቶች መሣሪያቸውን ከልጆቻቸው እንዲያርቁ እና እንዲቆልፉበት ያዛል።

ሐሙስ በዩቲዩብ ላይ በተጫነ የቪዲዮ መልዕክት፤ የትምህርት ቤቱ የበላይ ተቆጣጣሪ ቲም ትሮን ሲናገሩ ልጁ እና ወላጆቹ ወደ ቢሮ ተጠርተው ሁኔታው ሲነገራቸው "ምንም አይነት ተግሳጽ አልነበረም" ብለዋል።

ትምህርት ቤቱ "የጦርነት ቀጠና" እንደሚመስል እና ለሳምንታት ዝግ ሆኖ እንደሚቆይም ተናግረዋል።

ዋና ዐቃቤ ሕጓ ማክዶናልድ አርብ ዕለት ጀምስ ክሩምብሌይ ስለ ጥቃቱ ሲሰማ ለባለሥልጣናት ከማሳወቁ በፊት "መሣሪያውን ለማየት በቀጥታ ወደ ቤቱ በመኪና ሄዷል" በማለት ልጁ ወንጀለኛ መሆኑን መጠርጠሩን ተናግሯል።

"እንደ እናት፣ እንደ ዐቃቤ ሕግ፣ በዚህ አውራጃ እንዳለ ነዋሪ ተናድጃለሁ" የሚሉት ዋና ዐቃቤ ሕጓ፤ "ጥቃቱን ለማስቀረት "በጣም ቀላል እና ብዙ ነገሮች ነበሩ" ሲሉ ገልጸዋል።

ባለፈው ረቡዕ ዐቃቤ ሕጎች ልጁን እንደ አዋቂ ሰው የሽብርተኝነት እና የአንደኛ ደረጃ ግድያ ክስ መስርተውበታል።

ዋና ዐቃቤ ሕጓ የክሱን ሂደት በተናገሩበት ወቅት እንደገለጹት ተጠርጣሪው ጥቃቱን "ከአደጋው ቀደም ብሎ" እንዳቀደው የሚያሳዩ "ብዙ ዲጂታል ማስረጃዎች" በቢሯቸው አሉ።