በማሊ ታጣቂዎች አውቶብስ ላይ በተፈጸመ ጥቃት በርካታ ሰዎች ተገደሉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በማዕከላዊ ማሊ ታጣቂዎች ሲቪሎችን አሳፍሮ ወደ ገበያ ሲሄድ በነበረ አውቶብስ ላይ በፈጸሙት ጥቃት ቢያንስ 31 ሰዎች መገደላቸውን የአካባቢው ባለሥልጣናት ገለጹ።
ማንነታቸው ያልታወቁ ታጣቂዎች አውቶብሱ ላይ ጥቃት ሲከፍቱ የመጀመሪያ ኢላማቸው አሽከርካሪው የነበረ ሲሆን ወዲያው ገድለውታል።
የጥቃቱ አብዛኞቹ ሰለባዎች ወደ ገበያ ለሥራ በማምራት ላይ የነበሩ ሴቶች እንደሆኑ የአካባቢው ምንጮች ለአንድ የዜና ወኪል ተናግረዋል።
ጥቃቱ በአገሪቱ በፍጥነት እየተባባሰ በመጣው የጂሃዲስት አማጽያን የተፈጸመ ነው ተብሏል።
የታጠቁ ሰዎች "የተሽከርካሪው ጎማ ላይ ተኩሰው ያስቆሙት ሲሆን በሰዎች ላይ ተኩሰዋል" ሲሉ ጥቃቱ ከተፈጸመበት ስፍራ አቅራቢ የሚገኘው የባንካስ ከተማ ከንቲባ ሙላይ ጊንዶ ለሮይተርስ የዜና ወኪል ተናግረዋል።
ሌሎች ተጨማሪ ሰዎች ወይ ጠፍተዋል ወይ ቆስለዋል ሲሉም ተናግረዋል።
ጥቃቱን ተከትሎ በማኅበራዊ ድረ ገጾች ላይ እየተዘዋወሩ ያሉ አሰቃቂ ምስሎች አውቶቡሱ አሁንም በሟቾች ተሞልቶ ሲጨስ ቢያሳይም ቢቢሲ የምስሎቹን ትክክለኝነት በራሱ ማረጋገጥ አልቻለም።
የጥቃቱ ኢላማ የሆነው አውቶብስ በሳምንት ሁለት ጊዜ ከሶንጎ መንደር በ10 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወደምትገኘው ባንዲያጋራ ገበያ ሰዎችን የሚያጓጉዝ ሲሆን በዚህ ጉዞ ላይ ሳለ ነበር ለጥቃት የተዳረገው።
ጥቃቱ የተፈጸመው ከቅርብ ወራት ወዲህ ከአልቃይዳ እና ከእስላማዊ መንግሥት ቡድን ጋር ግንኙነት ባላቸው አማጺያን የተቀሰቀሰው ግጭት ተባብሶ በቀጠለባት የምዕራብ አፍሪካ አገር ማሊ፣ ሞፕቲ በተሰኘው ግዛት ማዕከል ላይ ነው።
በግንቦት ወር የቀድሞውን አስተዳደር ከሥልጣን አስወግዶ የተቋቋመው የማሊ የሽግግር መንግሥት ስለ ጥቃቱ እስካሁን የሰጠው መግለጫ የለም።
ይህ ጥቃት የተፈጸመው ታጣቂዎች በአገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የተሽከርካሪዎች አጀብ ላይ ጥቃት በመሰንዘር አንድ ሲቪል ሠራተኛን ገድለው ሌላኛውን ማቁሰላቸው ከተሰማ ከአንድ ቀን በኋላ ነው።
በ16 ወራት ውስጥ ሁለት ጊዜ ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት በተደረገባት ማሊ፤ ፈረንሳይ በ5,100 ወታደራዊ ሠራዊት አማካኝነት የነበራትን የጋራ ወታደራዊ ዘመቻ አቁማለች።
ይህም ማዕከላዊ መንግሥቱ እንዲዳከም አስተዋጽኦ ያደረገ ሲሆን በማሊ የጂሃዲስቶች ጥቃቶች እንዲባባሱም አድርጓል።
ታዲያ በአገሪቱ ያለው አስከፊ የጸጥታ ሁኔታ የማሊ ማዕከላዊ መንግሥት ለእርዳታ ወደ ሩሲያው ቅጥረኛ ቡድን ዋግነር እንዲያማትር እንዳደረገው ተዘግቧል።












