በቅርቡ ሕይወቷ አልፎ የተገኘችው የቢቢሲ ሰራተኛ ቤተሰቦች ኬትን " ዓለምን ያደመቀች" ሲሉ አሰቧት

የፎቶው ባለመብት, Peter Mitchell
በኬንያ ሕይወቷ አልፎ የተገኘችው የቢቢሲ ሰራተኛ ወንድም "አስደናቂ አቅም" ለነበራት እህቱ ያለውን አድናቆትና ክብር ገለጸ።
ወንድሟ ፒተር ሚሸል ለቢቢሲ ሚዲያ አክሽን ትሰራ የነበረችው እህቱ ኬት በአፍሪካ ያሉ ማሕበረሰቦችን ለመርዳት ትልቅ ቁርጠኝነት እንደነበራት ተናግሯል።
ፖሊስ የ42 ዓመቷን ኬት አማሟት እየመረመረ መሆኑን ገልጿል።
ወንድሟ ፒተር" እህቴ ራሷ በማሕበረሰቡ ውስጥ በመሳተፍ ብቻ አይደለም ዓለምን ብሩህ ያደረገችው፤ በቁሳቁስም ቢሆን አሻሽለዋለች" ሲል ተናግሯል።
ቢቢሲ ሚዲያ አክሽን የቢቢሲ ዓለም አቀፍ የረድኤት ድርጅት ክንፍ ሲሆን፤ መገናኛ ብዙኃንን እና ኮሚኒኬሽንን በመጠቀም ለእኩልነትን የሚሰራ ነው።
በሰሜን ምስራቅ ኢንግላንድ ዋይትሊይ ቤይ ያደገችው ኬት በቅርቡ በኢትዮጵያ አዲስ አበባ በሚገኘው ድርጅቱ መሥሪያ ቤት እየሰራች ነበር።
ኬት ባለፈው ሳምንት አርብ ዕለት ነበር በኬንያ መዲና ናይሮቢ በሚገኝ ሆቴል ሕይወቷ አልፎ የተገኘችው።
ወንድሟ ለቢቢሲ ሲናገር "ዛምቢያ፣ ደቡብ ሱዳን ፣ ናይጄሪያ ፣ ኢትዮጵያ በሄደችበት ሁሉ ሁልጊዜ ፕሮጀክቶችን በመምራት እና የገንዘብ ድጋፎችን በማፈላለግ እየሰራች ነበር" ብሏል።
ፒተር አክሎም እህቱ ኬት ከሰዎች ጋር የመግባባት እና የሁሉም ሰው ጓደኛ የመሆን አስገራሚ ተፈጥሯዊ ችሎታ እንደነበራት ተናግሯል።
" ሁሉም ሰው እያጽናናን ነው፤ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ጓደኞች ነበሯት። እስከዛሬ ሰምቻቸው ከማላውቃቸውና ከሚወዷት ሰዎች መልዕክቶች እየደረሱኝ ነው" ብሏል።
ፒተር ስደተኞች ላይ ፣ የሴቶች ጤና እና ደህንነት እንዲሁም ወጣቶች ላይ ለመስራት የተለየ ፍላጎት እንደነበራት ያስታውሳል።
ኬት በጣም ደፋር እና ሁል ጊዜ በጣም አስቸጋሪ የሚባሉ ሥራዎችን በአስቸጋሪ ቦታዎች ለመስራት ፈቃደኛ ነበረችም ብሏል ፒተር።
ኬት በመጨረሻ ያቀረበችው የገንዘብ ድጋፍ ማመልከቻ የተሳካ ሲሆን በኢትዮጵያ ትምህርት ላይ ያተኮረ ፕሮጀክትን ተጠቃሚ ያደርጋል።
" በሚያሳዝን ሁኔታ ግን ኬት ይህንን የገንዘብ ድጋፍ ለመስማት አልታደለችም። ይህ ዜና የተሰማው በሳምንቱ መጨረሻ እርሷ ከሞተች በኋላ ነበር። ግን ይህ የመጨረሻዋ ትንሿ ድሏ ነው" ብሏል ፒተር።
ቀደም ብሎ ፒተር በመገናኛ ብዙኃንና በማህበራዊ ሚዲያዎች ሰዎች ስለ እህቱ ሞት የሚሰነዘሩ መላምቶችን ችላ እንዲሉ አሳስቦ ነበር።
ፒተር እህቱን ለመጨረሻ ጊዜ ከእናታቸው ጋር ሆኖ ያዋራት ከመሞቷ ከቀናት በፊት ነበር።
" እኛ ቅድሚያ የምንሰጠው ኬትን ወደ ቤት ማምጣት ነው፤ በማሕበረሰቡ ውስጥ ያለው ሰው ሁሉም ድንቅ ነበር። መመገብ ከምንችለው በላይ ሰዎች የሚያመጡት ምግብ ተትረፍርፏል። በርካታ አበቦችንና ካርዶችን እየተቀበልን ነው" ብሏል ፒተር
የቢቢሲ ሚዲያ አክሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ካሮላይን ነርሲ በመግለጫቸው "በጣም የምትወደድ ሰራተኛ ነበረች በድርጅቱም ለ14 ዓመታት አገልግላለች። በመላ ድርጅቱ የምትታወቅ በተለይ ደግሞ ኢትዮጵያ ፣ ደቡብ ሱዳን ፣ ዛምቢያ እና ለንደን ባሉ ሰራተኞች እጅግ ተወዳጅ ነበረች" ብለዋል።












