የኬንያ ፖሊስ የቢቢሲ ሠራተኛን ሞት መመርመር ጀመረ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የኬንያ ፖሊስ አንዲት የቢቢሲ ሠራተኛ በኬንያ መዲና ናይሮቢ ሞታ መገኘቷን ተከትሎ ምርመራ መጀመሩን አስታውቋል።
የብሪታኒያ ዜግነት ያላት ኬት ሚሸል በተለያዩ የአፍሪካ አገራት እየተዘዋወረች ለቢቢሲ ሚድያ አክሽን ሰርታለች።
ቢቢሲ ሚዲያ አክሽን የቢቢሲ ዓለም አቀፍ የረድኤት ድርጅት ክንፍ ሲሆን፤ መገናኛ ብዙኃንን እና ኮሚኒኬሽንን በመጠቀም ለእኩልነትን የሚሰራ ነው።
የኬት ሚሼል ሞት ከሥራዋ አሊያም ከአሠሪዋ ከቢቢሲ ጋር ግንኙነት አለው ተብሎ አይታሰብም።
ምንም እንኳ እስካሁን ኬት የሞተችበት ምክንያት ግልፅ ባይሆንም ፖሊስ ግን ኬት ሕይወቷ ያለፈው በሰው ተገድላ ሊሆን ይችላል በሚል ምርመራ እያደረገ እንደሆነ ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ተናግሯል።
"የሚጠረጠረው ግለሰብ [በግድያው]. . . የሆቴሉ ጥበቃዎች እንዳይዙት በማሰብ ከሆቴሉ ስምንተኛ ፎቅ በመስኮት በኩል ዘሏል" ሲሉ የናይሮቢ ፖሊስ አዛዥ አውገስቲን ንቱምቢ ተናግረዋል።
በግድያ የሚጠረጠረው ግለሰብ ከሕንጻው ላይ መዝለሉን ተከትሎ ሕይወቱ አልፏል።
ሚሼል በቅርቡ በአዲስ አበባ በሚገኘው የቢቢሲ ሚድያ አክሽን ቢሮ ስታገለግል ነበር።
"በተፈጠረው ነገር እጅግ ደንግጠናል፤ አዝነናልም" ብለዋል የቢቢሲ ሚድያ አክሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ካሮላይን ነርሲ ባወጡት መግለጫ።
"ኬት በጣም ተወዳጅ የሥራ ባልደረባችን ነበረች። በነባር ፕሮጀክት አስተዳዳሪነት ስታገለግል ነበር። ከእኛ ጋር ለ14 ዓመታት ቆይታለች። በድርጅቱ እጅጉን ታዋቂ ነበረች። በተለይ ደግሞ ኢትዮጵያ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ዛምቢያ፣ እንዲሁም ለንደን ባሉ ባለደረቦቿ ትወደድ ነበር።"
"ለቤተሰቦቿና በመላው ዓለም ላሉ ጓደኞቿ መፅናናትን እንመኛለን" ብለዋል የቢቢሲ ሚድያ አክሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ካሮላይን ነርሲ።












