ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በኢትዮጵያ የሳንባ ምች ለህፃናት ሞት ቀዳሚ ምክንያት መሆኑ ተገለጸ
በዓለም አቀፍም ሆነ በኢትዮጵያ ደረጃ ለበርካታ ህፃናት ሞት ምክንያት ከሚሆኑ በሽታዎች መካከል የሳንባ ምች ቀዳሚው እንደሆነ ተገለጸ።
የጤና ሚኒስቴር በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ላይ ባወጣው መረጃ እንዳመለከተው በኢትዮጵያ በዓመት 36 ሺህ የሚሆኑ ህፃናት እድሜያቸው 5 ዓመት ሳይሞላ በሳንባ ምች በሽታ ይሞታሉ።
ከዚህም ጋር ተያይዞ "የአየር ብክለትን በመቀነስ፣ መሠረታዊ የጤና እና የሥርዓተ ምግብ አገልግሎቶች ጥራትን በማሻሻል በሳምባ ምች የሚሞቱ ህፃናትን እናትርፍ" በሚል መሪ ቃል የዓለም የሳንባ ምች ቀን በጅግጅጋ ከተማ ተከብሯል።
የሶማሌ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ መሐሙድ መሐመድ አብዲ በዕለቱ እንደተናገሩት በባለድርሻዎች ቅንጅታዊ ርብርብ ከህፃናት ሳንባ ምች በሽታ ጋር ተያይዞ ይደርሱ የነበሩ ችግሮች ላይ መሻሻሎች አሉ ብለዋል።
ከአምስት ዓመት እድሜ በታች የሚከሰተውን ሞትን ለመቀነስ እየተሰራ ያለውን ጥረት እንዲጠናከርም ጥሪ ቀርቧል።
ባለፉት ዓመታት የህፃናትን ሞት ለመከላክል በተደረገው ጥረት በአውሮፓውያኑ 2005፣ ከ1000 በህይወት ከሚወለዱት ህፃናት ውስጥ 123 የሚሆኑት በሳንባ ምች ይሞቱ ነበር።
ይህም አሀዝ በአውሮፓውያኑ 2019 ወደ 59 ዝቅ ማድረግ መቻሉን በጤና ሚኒስቴር የእናቶችና ህፃናት ጤና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር መሰረት ዘላለም በመድረኩ ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ አንድ ሺህ በህይወት ከሚወለዱ ህጻናት ከ5 ዓመት በታች የሞት ምጣኔ ሲታይ ከፍተኛው በሶማሌ ክልል 101 እና ዝቅተኛው በአዲስ አበባ 26 የተመዘገበባቸው መሆኑ ተገልጿል።
የአየር ብክለትን በመቀነስ፣ የግልና የአካባቢ ንጽሕናን በመጠበቅ፣ ንጹህ የውሃ አቅርቦትን በማሻሻል በሳምባ ምች ምክንያት ህፃናት ላይ የሚደርሰውን ሞት ሃምሳ በመቶ መቀነስ እንደሚቻል በወቅቱ የቀረቡ ጥናታዊ ጽሑፎች አመልከተዋል።