በስህተት የታሰረው ጥቁር አሜሪካዊ ከ42 ዓመት እስር በኋላ ነፃ ወጣ

ኬቨን ስትሪክላንድ

የፎቶው ባለመብት, Midwest Innocence Project

ታትሟል

ሁኔታው የተከሰተው በአውሮፓውያኑ 1978 ሲሆን የሚዙሪ ነዋሪ ኬቨን ስትሪክላንድ በሶስት ግድያዎች ተከሶ የ50 ዓመት እስር ተፈረደበት።

ከሰሞኑም የተፈረደበት በስህተት ነው በሚል ከ42 ዓመት እስር በኋላ ነፃ ወጥቷል።

በአሁኑ ሰዓት የ62 አመት ግለሰብ የሆነው ኬቨን ከታሰረበት ከ18 አመቱ ጀምሮ የተፈረደበትን ወንጀል እንዳልፈፀመና ንፁህ ነኝ ሲልም ቆይቷል።

ለአራት አስር አመታት በግፍ የታሰረው ኬቨን ከተለቀቀም በኋላ "ይህ ቀን ይመጣል ብዬ አላሰብኩም ነበር" ብሏል።

በግዛቲቷ ታሪክ ውስጥ ረጅሙ የተሳሳተ እስራት ቢሆንም በሚዙሪ ህግ መሰረት ምንም አይነት የገንዘብ ካሳ የማግኘት ዕድሉ አነስተኛ ነው።

በብሄራዊ ደረጃ ከአውሮፓውያኑ 1989 ጀምሮ ነፃ የወጡ ሰዎች መዝገብ መረጃ እንደሚያመለክተው የኬቨን ሰባተኛው ረጅሙ የተሳሳተ ፍርድ ነው።

በያዝነው ሳምንት ማክሰኞ አንድ ዳኛ ከ15 ሺህ 487 ቀናት እስር በኋላ ኬቨን በአስቸኳይ ከእስር እንዲለቀቅ አዘዋል።

ኬቨንን ከእስር ለማስለቀቅ ለወራት የጣሩት የሚድዌስት ኢነሰንስ ፕሮጄክት ጠበቆች ለቢቢሲ እንደተናገሩት በዜናው በጣም መደሰታቸውን ነው።

"ማስረጃውን የተመለከተ ማንኛውም ዳኛ የኬቨንን ንፅህና እንደሚያረጋግጥ ፅኑ እምነት ነበረን እናም የሆነው ያ ነው" በማለት የሚድዌስት ኢነሰንስ ፕሮጄክት የህግ ዳይሬክተር ትሪሺያ ሮጆ ቡሽኔል በሰጡት መግለጫ

ዳይሬክተሯ አክለውም " የጠፋውን 43 አመት ማንም መልሶ አይሰጠውም። ላጣውና ለተወሰዱበት አመታቶች ቤሳ ቤስቲን ካሳ ወደማይከፍለው ግዛት ይመለሳል፤ ይህ ፍትህ አይደለም" ብለዋል።

ግዛቲቷ በዲኤንኤ (ዘረ መል) ማስረጃ ለተፈቱ እስረኞች ብቻ ሲሆን ካሳ የሚከፍለው በአይን እማኞች ምስክርነት የተፈቱ ግን ለካሳው መስፈርት እንደማያሟሉ ሚድዌስት ኢነሰንስ ፕሮጀክት ያስረዳል።

ኬቨን በአውሮፓውያኑ 1978 በካንሳስ ከተማ ከተፈጸመው ዘረፋና ግድያ ጋር ተያይዞ የ50 ዓመታት ፅኑ እስራት ተፈርዶበታል።

በዚያች ምሽት አራት ታጣቂዎች በአንድ ቤት ውስጥ ሰብረው በመግባት ሶስት ሰዎችን ተኩሰው ገደሉ።

በቤቱ ውስጥ የነበረች ሲንቲያ ዳግላስ የተባለች አራተኛ ተጎጂ የሞተች በማስመል ቆስላ ተርፋለች።

የተጎጂዋ እህት የወንድ ጓደኛ በሰጠው ጥቆማ ኬቨን በቁጥጥር ስር የዋለ ሲሆን ግለሰቧም ወንጀለኛውን ለመለየት ከተጠርጣሪዎች መካከል እሱን ለይታ እንድታወጣ ግፊት መደረጉም ተዘግቧል።

ኬቨን በበኩሉ ወንጀሉ በተፈፀመበት ወቅት በቤቱ ውስጥ ቴሌቪዥን ሲመለከት እንደነበር ለፖሊስ ተናግሯል። ፈፅሟል ለተባለው ወንጀልም ሆነ ከወንጀሉ ጋር የሚያይዘው ምንም አይነት ተጨባጭ ማስረጃ አልቀረበም።

በአውሮፓውያኑ 1979 የመጀመሪያ ችሎት ላይ ከነበሩት 12 አቃብያነ ህግ መካከል አንደኛው ጥቁር አቃቤ ህግ ነፃ እንዲወጣ መጠየቁን ተከትሎ ለሁለተኛ ችሎት ተመርቷል።

በሁለተኛው ችሎት ላይ ሁሉም አቃብያነ ህግ ነጮች የነበሩ ሲሆን በአንደኛው ወንጀል በመጀመሪያ ደረጃ ግድያ እንዲሁም በሁለት ወንጀሎች በሁለተኛ ደረጃ ግድያ ጥፋተኛ ሆነው አግኝተውታል።

ከአመታት በኋላ ብቸኛ ምስክርነት ሰጥታ የነበረችው ሲንቲያ "ያኔ ነገሮች ግልፅ አልነበሩም፤ በአሁኑ ወቅት ግን የበለጠ ስለማውቅ ይህንን ሰው ከቻልኩ መርዳት እፈልጋለሁ" በማለት ለሚድዌስት ኢነሰንስ ፕሮጄክት ፅፋለች።

ሆኖም ሲንቲያ በኬቨን ላይ የሰጠችውን የመጀመሪያ ምስክርነት ቃልን በመሻር ሌላ ቃል ከመስጠቷ በፊት ህይወቷ አለፈ ነገር ግን እናቷ፣ እህቷ እና ሴት ልጇ " የተሳሳተ ሰው" ለይታ ማውጣቷን ለፍርድ ቤት መስክረዋል።

ኬቨን ስትሪክላንድ በታዳጊነቱ

የፎቶው ባለመብት, Midwest Innocence Project

የምስሉ መግለጫ, ኬቨን ስትሪክላንድ ከአባቱ ጋር በታዳጊነቱ