ዓለም አቀፉ የጌጣጌጦች ዘራፊ ቡድን አባላት እስራት ተፈረደባቸው

ታትሟል

በተለይ ታዋቂ ሰዎች ላይ በማነጣጠር የሚታወቁት እና 26 ሚሊዮን ፓውንድ የሚያወጡ ውድ ጌጣጌጦችን የሰረቁት ዘራፊዎች እስራት ተፈረደባቸው።

ጁጎስላቭ ጆቫኖቪክ፣ አሌሳንደሮ ማልቴሴ እና አሌሳንድሮ ዶናቲ የተሰኙት ዘራፊዎች የፎርሙላ ዋን የመኪና ውድድር ሥራ አስፈጻሚ ልጅ የሆነችው የታማራ ኢክሊስተን መኖሪያ ቤትን መዝረፋቸውን አምነዋል።

ሦስቱ ጣሊያናዊያን በምዕራባዊ ለንደን የሚገኘውን የቼልሲው ተጫዋች ፍራንክ ላምፓርድን መኖሪያ ቤት እንዲሁም በህይወት የሌሉት የላንካስተር ሲቲ ሊቀ መንበር የነበሩትን ቪቻዪ ስሪቫዳንፐራባ ቤቶችን በመዝረፍም ጥፋተኛ ተብለዋል።

በአጠቃላይም የ28 ዓመት የእስር ቅጣት ተጥሎባቸዋል።

ችሎቱ ጂዮቫኒክ የተሰኘውን የ24 ዓመት ግለሰብ በዘረፋ ወንጀል ለመሳተፍ በማሴር በሚል የዘጠኝ ዓመት እስር ሲፈርድበት በሕገወጥ መንገድ የተገኘ ገንዘብን ሕጋዊ አስመስሎ በማቅረብ ወንጀል ደግሞ ተጨማሪ ሁለት ዓመት ፈርዶበታል።

የ45 ዓመቱ ዶናቲም በተመሳሳይ ለዘረፋ ወንጀል በማሴር ስምንት ዓመት ከዘጠኝ ወር እንዲታሰር ተፈርዶበታል።

እ.ኤ.አ. በ2019 የታኅሣሥ ወር የመጀሪያ በ13 ቀናት ውስጥ ብቻ ከሦስቱ ዝነኛ ሃብታሞች ቤት 25 ሚሊዮን ፓውንድ የሚያወጡ ጌጣ ጌጦችን ዘርፈዋል። ከተዘረፉት ውድ ጌጣጌጦች እና ሰዓቶች መካከልም አብዛኞቹ አልተገኙም።

ጉዳዩን የያዙት ዐቃቤ ሕግ ቲሞቲ ክሬይ እንደተናገሩት ይህ የዘራፊ ወንበዴዎች ቡድን በዩናይትድ ኪንግደም ታሪክ ውስጥ ከታዩ የዘረፋ ወንጀሎች ውስጥ ከፍተኛው ነው ብለዋል።

"ዘራፊዎቹ ጥንቃቄ የተሞላበት ጥናት እንዲሁም ዝግጅት አድርገዋል። በተለይም በዘረፋው ሰለባ የሆኑት ሰዎችን ካላቸው ሃብት ብሎም ዝና ጋር ተያይዞ ኢላማ ውስጥ ገበተዋል" ሲሉም አክለዋል።

ዐቃቤ ሕጉ ጨምረው እንደተናገሩት ዘረፋው ከመካሄዱ 15 ቀናት ገደማ ቀደም ብሎ ጂዮቫኒክ አንድ ዳንኤል ቩኮቪች ከተባለ ግለሰብ ጋር ከስቶክሆልም ወደ ለንደን ተጉዘው ገብተዋል። እንዲሁም ጂዮቫኒክ በቡድኑ ዕዝ ውስጥ ሁለተኛ ሰው ሲሆን ቩኮቪች ዋናው አንቀሳቃሽ እንደሆነ ተናግረዋል።

ቩኮቪች እስካሁን ድረስ በቁጥጥር ስር ያልዋለ ሲሆን ሰርቢያ ውስጥ ይገኛል ተብሎም ይታመናል። ቢቢሲ በግለሰቡ ላይ በሰራው ምርመራ መሰረት ቢያንስ 19 የተለያዩ የማንነት መለያዎች እንዳሉት ታውቋል።