ጋና ከኢትዮጵያ ጋር አቻ በመለያየቷ ለዓለም ዋንጫ የማለፍ እድሏ አጣብቂኝ ውስጥ ገባ

አንድሬ አዩ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

ጋና ለዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ከኢትዮጵያ ጋር ያካሄደችውን ጨዋታ አንድ አቻ መለያየቷን ተከትሎ ኳታር ለሚካሄደው የዓለም ዋንጫ ውድድር የማለፍ እድሏ አጣብቂኝ ውስጥ ገብቷል።

የጋና ብሔራዊ ቡድን አምበል አንደሬ አዩ በመጀመሪያው አጋማሽ ከቅጣት ምት አስደናቂ ጎል ያስቆጠረ ሲሆን በሁለተኛ አጋማሽ ላይ የኢትዮጵያ ብሔራዊ አምበል ጌታነህ ከበደ ኢትዮጵያን አቻ ማድረግ ችሏል።

በመድቡ 4 ነጥብ ብቻ ያላቸው ዋሊያዎቹ ቀድሞውኑ ከውድድሩ ውጪ መሆናቸው የተረጋገጠ ሲሆን፤ 9 ነጥብ የነበራት ጋና ግን ከኢትዮጵያ ጋር የነበራትን ጨዋታ አሸንፋ ለዓለም ዋንጫ ውድድር ተሳታፊነት ግስጋሴዋን የምታቀናበት ጨዋታ ይሆናል ተብሎ ተጠብቆ ነበር።

ይሁን እንጂ በአሁኑ ወቅት ዓለም አቀፍ ደረጃን የጠበቀ ስታዲየም የላትም ተብላ በደቡብ አፍሪካ ለመጫወት የተገደደችው ኢትዮጵያ ከጋና ጋር ነጥብ ተጋርታለች።

ጋና እና ኢትዮጵያ በሚገኙበት ምድብ ደቡብ አፍሪካ አንድ ጨዋታ እየቀራት 10 ነጥብ ያላት ሲሆን፤ ዚምባብዌ በተመሳሳይ አንድ ቀሪ ጨዋታ እያለት በ1 ነጥብ መጨረሻ ላይ ተቀምጣለች።

ደቡብ አፍሪካ ዛሬ ምሽት አራት ሰዓት ላይ ዚምባብዌን በሜዳዋ የምታስተናግድ ሲሆን፤ ደቡብ አፍሪካ ይህን ጨዋታ የምታሸንፍ ከሆነ ምድቡን በአንድኛነት ትጨርሳለች።

የአፍሪካ አገራት በ10 ምድብ ሲጫወቱ የቆዩ ሲሆን፤ ከየምድቡ አንደኛ ሆነው የሚጨርሱት ከአራት ወራት በኋላ በደርሶ መልስ ተለይተው አምስት አገራት ኳታር ለምታዘጋጀው የዓለም ዋንጫ አፍሪካን ወክለው ይቀርባሉ።

እስካሁን ድረስ ማሊ፣ ግብፅ፣ ሴኔጋል እና ሞሮኮ ከምድባቸው በአንደኛነት ማለፋቸውን ያረጋገጡ አገራት ናቸው።