ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኦቲዝም ያለበት ግለሰብ ከ15 ዓመታት ሆስፒታል ቆይታ በኋላ ወደቤቱ ተሸኘ
ግማሽ የህይወት ዘመኑን ለሚጠጋ ጊዜ በአእምሮ ሆስፒታል ውስጥ ያሳለፈው የኦቲዝም እክል ያለበት ግለሰብ እናቱ ባደረገችው ያላሰለሰ ዘመቻ በግዴታ ገብቶበት ከነበረው ሆስፒታል እንዲወጣ ተደረገ።
የ32 ዓመቱ ሪያን ክላርክ ከአውሮፓውያኑ 2006 ጀምሮ በሆስፒታል ውስጥ ነበር።
ከ15 ዓመታት በኋላ ወደ ቤቱ የተመለሰው ሪያን ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማው እናቱ ሻሮን ተናግራለች።
በሐምሌ ወር ላይ ብሔራዊ የኦቲስቲክ ማኅበረሰብ (ኤንኤኤስ) በእንግሊዝ ውስጥ በአእምሮ ሆስፒታሎች የታጎሩ የኦቲዝም ተጠቂ ሰዎች ቁጥር "ብሔራዊ ቅሌት" ነው ብሎታል።
ሪያን ክላርክ በወቅት የአዕምሮ ሆስፒታል እንዲገባ የተደረገበት ምክንያት ራሱን ይጎዳል በሚል ስጋት ነው።
ታዳጊው በመጀመሪያ በተደረገለት ምርመራ የአእምሮ ህመም አንዱ በሆነው የስኪዞፈሪንያ ተጠቂ ነው ቢባልም ከአራት ዓመት በፊት በነበረው ውጤት ግን አንደኛው የኦቲዝም አይነት እንደሆነም ተገልጿል። በወቅቱ 28 ዓመቱ ነበር።
እስካለፈው ሰኞ ድረስ ያለፉትን አምስት ዓመታት በወንጀል የተፈረደባቸው የአእምሮ ህሙማን ታካሚዎችን በሚንከባከብ በፎረንሲክ ሳይካትሪ ክፍል ውስጥ ነው ያሳለፈው።
ልጇ በመለቀቁ ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማው የተናገረችው እናት ቀጣይ ህይወቱንም በተመለከተ ራሱን ችሎ ከተንከባካቢዎች ጋር እንደሚኖር አስረድታለች።
ዘላቂ የአእምሮ እድገት ውስንነት እክል የሆነውን ኦቲዝም ህፃናት ከማኅበራዊ ህይወታቸው መነጠል፣ ያልተለመደ ባህሪ ማሳየት፣ የተለየ የመማር ክህሎቶች እንዲኖራቸው ያደርጋቸዋል።
የዕድሜ ልክ የዕድገት እክል የሆነው ኦቲዝም ተጠቂዎች ላይ በተለያየ መንገድ ይጎዳል።
የኦቲዝም ተጠቂዎች በእንክብካቤ እጥረት፣ ቤተሰብ ወይም ተንከባካቢዎች መንከባከብ ሳይችሉ ወይም የአእምሮ ጤንነት ችግር ካለባቸው ነው ሆስፒታል የሚገቡት።
እናት ሻሮን ለ15 ዓመታት በአእምሮ ሆስፒታል ውስጥ ያሳለፈው ልጇን በተመለከተ ከፍተኛ ትግል ማድረጓንም ተናግራለች።
"የኦቲዝም ተጠቂ ነው፤ በአሁኑ ወቅት አንዳንድ ሃረጋትን ይደጋግማል ነገር ግን እሱ ሆስፒታል በነበረበት ጊዜ የመቋቋሚያ ዘዴው ነበር ብዬ አስባለሁ። አሁን ያ ሁኔታ የሚቆም ይመስለኛል። በጊዜም ሙሉ በሙሉ ያቆማል" ብላለች።
"ለወደፊቱ መጥፎ ቀናቶች ሊያጋጥሙት ይችላሉ ነገር ግን እየቀነሱ ይሄዳሉ" በማለት አስረድታለች።
ባለቤቷ ፒተር በበኩሉ የእንጀራ ልጁ "የተለመደ ህይወት" እንደሚኖረውና "በጣም ደስተኛ" እንደሆነ ተናግሯል።
"ቤት ሲመለስ ግራ ይጋባል ብለን አስበን ነበር፤ ነገር ግን ሁሉን ተቀብሎ በጣም ተደስቶ ሁሉንም ነገር በአንድ ጊዜ ለማድረግ እና በአንድ ጊዜ ለማየት ፈልጎ ነበር" ብሏል።
"እየሳቀ እና እየጨፈረ ነበር እናም በጣም ደስተኛ ሆኗል" በማለት አክሏል።
በ2015 እና 2021 መካከል በአእምሮ ሆስፒታል ውስጥ በአስገዳጅ ሁኔታ ያሉ ኦቲዝም ያለባቸው ቁጥር ከ1,105 ወደ 1,215 ከፍ ማለቱን የአገሪቱ ብሔራዊ ጤና ተቋም መረጃ ያሳያል።
የጤና እና ማኅበራዊ እንክብካቤ ክፍል በማኅበረሰብ አገልግሎቶች ላይ 62 ሚሊዮን ፓውንድ እንዳፈሰሰና ከሆስፒታሎች እንዲወጡም ያበረታታል።