የታዋቂው ሬጌ ባንድ ዩቢ40 መስራች አባል አስትሮ ህይወቱ አለፈ

አስትሮ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

እንግሊዛዊው ድምጻዊ፣ የታዋቂው ሬጌ ባንድ ዩቢ ፎርቲ (UB40) መስራች አባል ቴሬንስ ዊልሰን በ64 አመቱ ከዚህ አለም በሞት ተለየ።

አስትሮ በሚለው የመድረክ ስሙ የሚታወቀው ይህ ሙዚቀኛ ባደረባት ህመም ህይወቱ ማለፉን የአሁኑ ባንድ አረጋግጧል።

አስትሮ በሬጌ፣ ፖፕ ባንዱም ውስጥ ከሰላሳ ዓመታት በላይ ተጫውቷል።

"አስትሮን በማጣችን ተጎድተናል ልባችንም ተሰብሯል" ሲል በአሊ ካምቤል እና በአስትሮ የትዊተር አካውንት ላይ የወጣ መግለጫ አትቷል።

"አለም ያለርሱ አንድ አይነት ገፅታ አይኖራትም" የሚልም መልዕክት በትዊተር ገጹ ላይ ሰፍሯል።

አስትሮ ከታዋቂው ባንድ ዩቢ40 በአውሮፓውያኑ 2013 በመውጣት ከሌላኛው የቀድሞ ባንድ አባል አሊ ካምፕፔል ጋር በመሆን አብረውም ሲዘፍኑ ነበር። በዚህም ዓመት በተለያዩ ኮንሰርቶች የተጫወቱ ሲሆን በመጪውም ዓመት የሙዚቃ ጉዞ ያደርጋሉ ተብሎ ተጠብቆ ነበር።

የብሪታንያ ሬጌ መለያ የሆነው ዩቢ ፎርቲ በዝና ማማ ላይ የተቀመጡት በ1980ዎቹ ሲሆን ኢትዮጵያም ውስጥ 'ሬድ ሬድ ዋይን'፣ 'ካንት ኸልፕ ፎሊንግ ኢን ላቭ' በተሰኙ ዘመን ተሻጋሪ ሙዚቃዎቻቸው ይታወቃሉ።

በበርሚንግሃም ከተማ የተመሰረተው ይህ ቡድን በወቅቱ መንግሥት የስራ አጦችን ጥቅማ ጥቅም ለማስጠበቅ በወጣው ቅፅም ነው የባንዳቸው ስያሜ የተሰጠው። ባንዱ ከ70 ሚሊዮን በላይ የአልበሞች ቅጅን በመሸጥ በዩናይትድ ኪንግደም ያሉ የሙዚቃ ሰንጠረዦችን ተቆጣጥረው ነበር።

የዩቢ40 ባንድ አባላት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

"ነፍስህን ያሳርፍ" በሚልም በአሁኑ ወቅት ያለው የዩቢ 40 ባንድ ትዊተር ገፅ ሃዘኑን አስፍሯል።

"የዩቢ40 የቀድሞ አባል ቴሬንስ ዊልሰን በህመም ምክንያት ከዚህ አለም በሞት መለየቱን ዛሬ ምሽት ሰምተናል።ለቤተሰቦቹ የተሰማንን ሀዘን እንገልፃለን።" ብሏል ባንዱ

ዩቢ 40 ባንድ በአጠቃላይ በዩኬ ምርጥ የሚባሉ 40 ነጠላ ዜማዎች፣ 40 አልበሞችን የሰሩ ሲሆን አስትሮም የባንዱ መሪ ዘፋኝ ነበር።