አፍጋኒስታን፡ ሰርግ ላይ ሙዚቃ መከፈቱ ያበሳጫቸው ታጣቂዎች ሁለት ሰዎችን ገደሉ

አፍጋኒስታን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

በአፍጋኒስታን የታሊባን አባላት ነን ያሉ ታጣቂዎች በአንድ የሰርግ ስነ ስርዓት ላይ ይጫወት የነበረ ሙዚቃ ለማስቆም በከፈቱት ተኩስ የሁለት ሰዎችን ህይወት ሲቀጥፉ አስር ሰዎችን ማቁሰላቸውን ባለስልጣናት ተናገሩ።

የታሊባን ቃል አቀባይ እንዳሉት ሁለቱ የታጠቁ ሰዎች በቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን ድርጊቱንም የእስላማዊ እንቅስቃሴውን በመወከል አልፈጸሙም ሲሉ አስተባብለዋል።

እ.ኤ.አ. ከ 1996 እስከ 2001 ታሊባን አፍጋኒስታንን በሚያስተዳድርበት ወቅት ሙዚቃ ማጫወትን ከልክሎ ነበር። ነገር ግን አዲሱ የታሊባን አስተዳደር ሙዚቃን በተመለከተ እስካሁን ያስተላለፈው ትዕዛዝ የለም።

አንድ የአይን እማኝ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ባሳለፍነው አርብ የአራት ሰዎች ሰርግ በጋራ ሱርክህ ሮድ በተባለ አካባቢ በመከወን ላይ ሳለ ነው ጥቃቱ የተፈጸመው።

ሰርገኞቹ ከአካባቢው የታሊባን መሪ ሙዚቃውን ለማጫወት ፈቃድ ጠይቀው ማግኘታቸውን እና ሙዚቃውም ሴት ታዳሚዎች ለብቻቸው ባሉበት ቦታ ላይ ብቻ ተከፍቶ እንደነበረም አስረድተዋል።

ወደ እኩለ ለሊት አካባቢ የታጠቁት ሰዎች ወደ ሰርግ ቤቱ በመምጣት የሙዚቃ ማጫወቻዎችን ለመሰባበር ሞከሩ። ታዳሚዎች ለምን በማለት ቁጣቸውን ሲገልጹ የታጠቁት ሰዎች ተኩስ መክፈታቸው ተነግሯል።

የታሊባን ቃል አቀባይ ዛቢሁላህ ሙጃሂድ ክስተቱ በምርመራ ላይ እንደሆነ ተናግረዋል።

ከታሊባን በተቃራኒ የቆመው የእስላማዊ መንግስት ቡድን በአካባቢው የሚንቀሳቀስ ሲሆን ከዚህ ቀደም በተመሳሳይ ድርጊቶች ይወነጀል ነበር።

ታሊባን ወደ ስልጣን መንበሩ ከተመለሰ በሗላ ቡድኑ አንድ ዘፋኝን ገድሏል እንዲሁም የሙዚቃ መሳሪያዎችን ሰባብሯል በሚል ይወነጀላል።

በርካታ የሙዚቃ መሳሪያ ተጫዋቾች ብሎም ዘፋኞች አፍጋኒስታንን ጥለው ተሰደዋል።