በስፔን ከበሬ የመሸሽ ፌስቲቫል ላይ የሰው ህይወት አለፈ

ታትሟል

በምስራቃዊ ስፔን ኦንዳ በተሰኘ ከተማ ከበሬ የመሸሽ ባህላዊ ጨዋታ ላይ አንድ የ55 አመት ግለሰብ በበሬ ቀንድ ተወግቶ ሕይወቱ አለፈ።

‘ፊራ ዴ ኦንዳ’ ተብሎ በሚጠራው ከጎሽ የተዳቀሉ በሬዎችን የመሸሽ ፌስቲቫል ላይ ተሳታፊ የነበረው ሟቹ ህይወቱን ለማትረፍ ወደ ሆስፒታል ቢወሰድም ሊሳካ አልቻለም።

በሰውዬው ህልፈት ምክንያት የፌስቲቫሉ አዘጋጆች ከበሬ የመሸሽ ጫወታዎችን በሙሉ መሰረዛቸው የገለጹ ሲሆን ሌሎቹ የፌስቲቫሉ ዝግጅቶች ግን እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

የኮቪድ ገደቦች መነሳትን ተከትሎ በስፔን ተመሳሳይ ዝግጅቶች መደረግ ከጀመሩ ወዲህ በዚህ ዓይነቱ ክስተት ሰው ሲሞት የመጀመሪያ እንደሆነም ተዘግቧል።

በስፔን ከበሬ የመሸሽ ጨዋታዎች ላይ የሰዎች ጉዳት ለመቀነስ በሚል የጨዋታ ህግ ለውጥ ተደርጎ ጥቂት ውድድሮች እየተደረጉ ቢሆንም ይህ ጨዋታ ከቶውንም መካሄድ አይገባውም የሚል ክርክርን ግን ጭሯል።

ይህ ዝግጅት በስፔን ለረዥም ጊዜ የቆየ ባህል ጨዋታ ሲሆን በአጎራባች ፈረንሳይ እና ፖርቹጋልም ተመሳሳይ ከበሬ የመሸሽ ጨዋታዎች ይካሄዳሉ።

ጨዋታው በአንድ ለዚህ ዓላማ በተዘጋጀ ስፍራ ላይ የተለቀቁ በርካታ ተሳታፊዎች ከጎሽ የተዳቀሉ በሬዎች ፊት ለፊት በመረሮጥ መሸሽ ነው።

በአንዳንድ ፌስቲቫሎች ደግሞ በሬዎቹ አወዛጋቢ በሆኑ የበሬ-ፍልሚያ ውድድሮች እንዲሳተፉ የሚደረግ ሲሆን በሰዎች ላይ ጉዳቶች ይከሰታሉ።

እንደ አውሮፓውያኑ ከ1910 ጀምሮ በፓምፕሎና በተከወኑ ጨዋታዎች ላይ ቢያንስ 16 ተሳታፊዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል።