የቻይና የሚሳኤል ሙከራ አሳሳቢ መሆኑን የአሜሪካ ከፍተኛ የጦር ጀነራል ተናገሩ

ታትሟል

የአሜሪካ ከፍተኛ የጦር ጀነራል ቻይና አደረገች የተባለው የሃይፐርሶኒክ ሚሳኤል ሙከራ የቀዝቃዛውን ጦርነት ከቀሰቀሰው የሶቭየት ሳተላይት ማምጠቅ-ስፑትኒክ ክስተት ጋር ይቀራረባል ሲሉ ተናገሩ።

የአሜሪካ የጦር አዛዦች ሊቀመንበር ማርክ ሚሌይ ከብሉምበርግ ኒውስ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ የቻይና ጦር በፍጥነት እያደገ ነው ብለዋል።

ቻይና ያደረገችው የሚሳኤል ሙከራ የአሜሪካን ጦር ማስደንገጡን ፋይናንሻል ታይምስ በዚህ ወር ዘግቧል።

ይሁን እንጂ ቻይና የሚሳኤል ሙከራ አላደረኩም፤ የጠፈር መንኮራኩር ነው ብላለች።

ጀነራል ሚሌይ ረቡዕ ዕለት ከብሉምበርግ ጋር በነበራቸው ቆይታ "ያየነው የሃይፐርሶኒክ ጦር መሣሪያ ሥርዓት ሙከራ በጣም ወሳኝ ክስተት ነው። ይህም በጣም አሳሳቢ ነው" ሲሉ ተናግረዋል።

ጀነራሉ አክለውም "ሙከራው የስፑትኒክ ቅጽበት መሆኑን አላውቅም፤ ግን ለዚያ የቀረበ ነው። ይህ ሁላችንም ትኩረት የምንሰጥበት ጉዳይ ነው" ብለዋል።

የጀነራሉ አስተያየት ቻይና በፈረንጆቹ ሞቃታማ ወቅት ሁለት የሚሳኤል ሙከራዎችን አድርጋለች ለሚለው ክስ በአሜሪካ ባለሥልጣናት የተሰጠ የመጀመሪያ አስተያየት ነው።

ሪፖርቶች እንደሚያመለክቱት ሚሳኤሉ ኒውክሌር የሚይዝ እና የአሜሪካ የአየር መከላከያ ዘዴዎችን ሊያመልጥ የሚችል ነው።

እአአ በ1957 ሶቭየት ያመጠቀችው ስፑትኒክ ሳተላይት ሶቭየት በቴክኖሎጂ አቅሟ የላቀች እየሆነች ነው በሚል አሜሪካውያንን አስደንግጦ ነበር።

በወቅቱ ሁኔታው ፕሬዚደንት ጆን ኤፍ ኬኔዲ አሜሪካ ሰዎችን ጨረቃ ላይ እንደምታሰርፍ እንዲያውጁ አስገድዷቸዋል። በእርግጥ ይህ ከአስር ዓመታት ባነሰ ጊዜ ውስጥ እውን ሆኗል።

የፔንታጎን ቃል አቀባይ ጆን ኪርቢይ ጀነራል ሚሌይ ረቡዕ ዕለት በተናገሩት ላይ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበዋል። "ይህ ለእኛ ያላሰብንበትና እንግዳ የሆነ ቴክኖሎጂ አይደለም" ብለዋል ቃል አቀባዩ።

ቃል አቀባዩ አክለውም አሜሪካ የመከላከል አቅሟን ለማጠናከር እየሰራች ሲሆን የራሷን ሃይፐርሶኒክ አቅሞች እየፈለገች ነው ብለዋል።

ሃይፐርሶኒክ ሚሳኤሎች ከድምጽ ፍጥነት በአምስት እጥፍ በሚልቅ ፍጥነት መጓዝ ይችላሉ።

ከተለመዱት ሚሳኤሎች የበለጠ የሚንቀሳቀሱና በአየር መቃወሚያ ለመጠለፍ አዳጋች የሆነ ብቃት ያላቸው ተደርገው ይወሰዳሉ።

ባለፈው ሳምንት አሜሪካ ቨርጂኒያ በሚገኘው የናሳ ተቋም ሦስት የሃይፐርሶኒክ ሚሳኤል ሙከራዎችን አድርጋለች።

ሙከራው ስለ ወደፊቱ የሃይፐርሶኒክ ሚሳኤል እድገት ለማሳወቅ እንደሚጠቅሙ የአሜሪካ ባለሥልጣናት በመግለጫቸው አስታውቀዋል።

ጀነራል ሚሌይ የቻይና ጦር እአአ በ1979 እጅግ በጣም ትልቅ በነበረውና በአርሶ አደር ላይ የተመሰረተ እግረኛ ጦር፤ ወደ ሁሉንም አካባቢዎች የሚሸፍን እና ዓለም አቀፋዊ ምኞቶች ወደሚሆን ወታደራዊ ኃይል ማደጓን አስጠንቅቀዋል።

እንደ ሲኤን ኤን ዘገባ የሲአይኤ ዳይሬክተር ቢል በርንስ ቻይና ባለፈው ሳምንት ለአሜሪካ ትልቅ የቴክኖሎጂ ስጋት መሆኗን ገልጸዋል።

ዳሬክተሩ በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ እንደተናገሩት የስለላ ተቋሙ ቻይናን ለመከታተል የሚያደርገውን ጥረት እንደሚያሳድግ ተናግረዋል።

የፕሬዚደንት ጆ ባይደን መሥሪያ ቤት የአሜሪካ እና የቻይና ግንኙነት እንደ አንድ "ስልታዊ ውድድር" መሆኑን ጠቅሷል።

ጀነራል ሚሌይ በትራምፕ አስተዳደር የመጨረሻ ጊዜያት ለቻይና አቻቸው አሜሪካ የኒዩክሌር ጥቃት እንደማትፈፅም ማረጋገጣቸው ከተገለጸ በኋላ በአገር ክህደት ተከሰው ባለፈው ወር ሥራቸውን እንዲለቁ ጥሪ ቀርቦባቸው ነበር።

ጀነራሉ በኋላ ላይ ጥሪዎቹ በሥራቸው ላይ ባለው "ተግባር እና ኃላፊነት ውስጥ ትክክል ናቸው" ብለዋል።