ሕጻናትን መግደሉን ያመነው እና ከእስር ቤት ያመለጠው ኬንያዊ ተገደለ

ታትሟል

ኬንያ ውስጥ በርካታ ሕጻናትን ስለመግደሉ ያመነው እና ከቀናት በፊት በመዲናዋ ናይሮቢ ከሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ ያመለጠው ተጠርጣሪ በተቆጡ ሰዎች በተፈጸመበት ድብደባ ተገደለ።

ማስተን ዋንጃላ የተባለው ተጠርጣሪ ረቡዕ ዕለት በ14 ሕፃናት የግድያ ወንጀል ፍርድ ቤት መቅረብ ይጠበቅበት ነበር። ይሁን እንጂ ተጠርጣሪው ከእስር ቤት አምልጦ ወደ ምዕራባዊ ኬንያ ከሸሽ በኋላ የአካባቢው ነዋሪዎች ይዘውት ድበደባ ከፈጸሙበት በኋላ ሕይወቱ አልፏል ተብሏል።

ፖሊስ እንዳለው በምዕራባዊ ኬንያ ቡንጎማ ተብላ የምትጠራ ከተማ ነዋሪዎች ማስተን ዋንጃላን ተከታትለው ከያዙት በኋላ በፈጸሙበት ድብደባ ሕይወቱ አልፏል።

ዋንጃላ ከ10 በላይ ሕፃናትን መግደሉን ያመነ ሲሆን ይህም በኬንያውያን ዘንድ ከፍተኛ ድንጋጤን እና ቁጣን ፈጥሮ ነበር።

ዋንጃላ ከሁለት ቀናት በፊት ከእስር ቤት ካመለጠ በኋላ ፖሊስ አጅግ አደገኛ ነው ያለውን ተጠርጣሪ መልሶ ለመያዝ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል።

የተጠርጣሪው ከእስር ቤት ማምለጥ በርካቶችን ያስቆጣ ሲሆን፤ የኬንያ ፖሊስ ዋና አዛዥ ከኃላፊነታቸው እንዲነሱ የሚጠይቁ ድምጾች በስፋት ተሰምተዋል።

ዋንጃላ ከእስር ቤት ማምለጡ የታወቀው ጠዋት በነበረው መደበኛ የታራሚዎች ቆጠራ ላይ ነበር። ጆጎ ሮድ ከተሰኘው ፖሊስ ጣቢያ ተጠርጣሪው ባመለጠበት ወቅት ተረኛ የነበሩ የፖሊስ መኮንኖች በቁጥጥር ሥር ውለዋል።

በቁጥጥር ሥር የዋሉት ሦስት የፖሊስ አባላት እስረኛው እንዲያመልጥ በመተባበር እና በቸልተኝነት ክስ ተመስርቶባቸዋል።