በአትሌት አግነስ ቲሮፕ ግድያ የተጠረጠረው ባለቤቷ በቁጥጥር ስር ዋለ

ታትሟል

በስለት ተወግታ የተገደለወችው የረዥም ርቀት ሯጯ አግነስ ቲሮፕ ባለቤት በኬንያ ፖሊስ በቁጥጥር ስር ውሏል።

በባሕር ዳርቻዋ ከተማ ሞምባሳ በቁጥጥር ስር የዋለው ኢማኑኤል ሮቲች ምርመራዎች ሲጠናቀቁ ክስ እንደሚቀርብበት አንድ የፖሊስ መኮንን ተናግረዋል።

የ25 ዓመቷ ቲሮፕ ረቡዕ ዕለት የአትሌቶች ተመራጭ የልምምድ ማዕከል በሆነችው ኢቴን ከተማ በሚገኘው መኖሪያ ቤቷ ነው ሞታ የተገኘችው።

ፖሊስ በአትሌቷ ግድያ ባለቤቷ ተጠርጣሪ ነው ብሎ ነበር።

አትሌቷ በቶኪዮ ኦሎምፒክ የ5 ሺ ሜትር ፍጻሜ አራተኛ ሆና አጠና ነበር። እአአ በ2019 በተካሄደው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በ10 ሺህ ሜትር የነሐስ አሸናፊም ነበረች።

የወንጀል ምርመራ ዳይሬክተር የሆኑት ጆርጅ ኪኖቲ ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል እንደገለጹት ባለቤቷ "ሲሸሽ" ከተያዘ በኋላ በእስር ላይ ይገኛል።

የተለያዩ አትሌቶች እና ተቋማት በቲሮፕ ሞተ የተሰማቸውን ጥልቅ እየገለጹ ነው።

የኬንያ የቀድሞ የአትሌቲክስ ቡድን አምበል ጁሊየስ ዬጎ ለቢቢሲ ወርልድ ሰርቪስ የኒውስዴይ ፕሮግራም "በእውነቱ በዓለም ላይ ካሉ ምርጥ አትሌቶች አንዷ ለመሆን ጠንክራ እየሠራች የነበረች አስገራሚ ወጣት ልጅ ነበረች" ብሏል።

ቲሮፕ በታዳጊነት ዘመኗ በ2012 እና 2014 የዓለም ሻምፒዮናዎች የ 5 ሺህ ሜትር የነሐስ አሸናፊ ነበረች። እአአ በ2015 የዓለም ሃገር አቋራጭ ሻምፒዮናም ሆናለች።

እአአ በ2017 እና በ 2019 የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናዎች ነሐስ አሸንፋለች። ከሁለት ወራት በፊት በቶኪዮ ኦሎምፒክ ከ 0.75 ሰከንዶች ከሜዳሊያዎች ውጭ ሆናለች።

ባለፈው ወር ጀርመን በተደረገ የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ሩጫ በ30 ደቂቃ 01 ሰከንድ የሆነ አዲስ የዓለም ክብረወሰን አስመዝግባለች።

ሐሙስ የኬንያ አትሌቲክስ ለቲሮፕ አክብሮቱን ለማሳየት ሁሉንም የአትሌቲክስ ውድድሮች ለሁለት ሳምንታት እንዲቋረጡ አዟል።

ረቡዕ ዕለት የዓለም አትሌቲክስ ፕሬዝዳንት ሴባስቲያን ኮ እና የዓለም አቀፉ የኦሎምፒክ ኮሚቴ አቻቸው ቶማስ ባህ ስለ ቲሮፕ ተናግረዋል።

የቀድሞው ድርብ የኦሎምፒክ ሻምፒዮናው ኮ "ባለፉት ስድስት ዓመታት ውስጥ ከታዩ የዓለም ምርጥ ሴት የረዥም ርቀት ሯጮች አንዷ" በማለት ገልጸዋታል።

አክለውም "አትሌቲክስ በጣም አሳዛኝ በሆነ ሁኔታ አንፀባራቂ ወጣት ኮከቡን አጥቷል። ይህ ለመላው የአትሌቲክስ ማህበረሰብ በተለይም ለቤተሰቦቿ፣ ለጓደኞቿ እና ለኬንያ አትሌቲክስ አስከፊ ነው" ብለዋል።

ባለፈው ወር ቲሮፕ በጀርመን በሚገኘው የስፖንሰር አድራጊዋ አዲዳስ ዋና መሥሪያ ቤት መቀመጫ የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ሩጫ የዓለም ክብረ ወሰን አስመዝግባለች። ግዙፉ የስፖርት ትጥቅ አምራች ኩባንያ በማህበራዊ ድር አምባ ሐዘኑን ገልጿል።