አትሌት አገንስ ቲሮፕ፡ ሞታ የተገኘችው ኬንያዊት አትሌት ባለቤት በፖሊስ ተጠርጥሮ እየታደነ ነው

አትሌት አገንስ ቲሮፕ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

በዓለም ክብረ ወሰን ባለቤቷ ኬንያዊት አትሌት አገንስ ቲሮፕ ሞት የተጠረጠረው ባለቤቷ እየተፈለገ መሆኑን ፖሊስ አስታወቀ።

አትሌት አገንስ በምትኖርበት የኬንያ ምዕራባዊት ከተማ ኢትን ቤቷ ውስጥ በስለት ተወግታ ነበር ሕይወቷ አልፎ የተገኘችው።

የሁለት ጊዜ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናዋ የነሐስ ሜዳልያ ተሸላሚ እና ከሁለት ወር በፊት በኦሊምፒክ ውድድር በ5 ሺህ ሜትር አራተኛ ደረጃ ይዛ ያጠናቀቀችው አትሌት አገንስ የ25 ዓመት ወጣት ነበረች።

ባለፈው ወር ቲሮፕ በጀርመን በተካሄደው የ10 ኪሎ ሜትር የሴቶች የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድርም የዓለም ክብረ ወሰንን ይዛለች።

የአትሌቷን ሞት ተከትሎም የወንጀል ምርመራ እየተደረገ ሲሆን ፖሊስ የአትሌቷ ባለቤት መሰወሩን አስታውቋል።

ማክሰኞ ዕለት ምሽት ልጃቸው እንደጠፋች የአትሌቷ አባት ለፖሊስ ካሳወቁ በኋላ ረቡዕ ዕለት የወንጀል መርማሪዎች በቲሮፕ ቤት ምርመራ ሲያካሂዱ እንደነበር ፖሊስ ገልጿል።

" ፖሊሶች ቤቷ ውስጥ ሲገቡ ቲሮፕን አልጋ ላይ ያገኟት ሲሆን በወለል ላይ ደም ተንጣሎ ነበር " ሲሉ የአካባቢው ፖሊስ ኃላፊ ቶም ማኮሪ ተናግረዋል።

ፖሊሶችም አትሌቷ አንገቷ ላይ በስለት እንደተወጋች እና ይህም ለሞት እንደዳረጋት አምነዋል።

ፖሊስ አክሎም የአትሌቷ ባለቤት በመሰወሩ በግድያ መጠርጠሩን የመጀመሪያ ደረጃ የምርመራ ሪፖርት አመልክቷል ብሏል።

ባለቤቷ በቲሮፕ ላይ የተፈጠረው ምን እንደነበር እንዲያስረዳ በፖሊስ እየታደነ ነው።

የፖሊስ ኃላፊው ማኮሪ አክለውም ፖሊስ በአትሌቷ ቤት ውስጥ ያለው የደህንነት ካሜራ [ሲሲቲቪ ካሜራ] ለምርመራ እንደሚረዳው እንደሚያምን ገልጸዋል።

ቲሮፕ በሆዷ አካባቢ በስለት ተወግታ ሞታ መገኘቷን ምንጮች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የኬንያ አትሌቲክስ ባወጣው መግለጫ " የኬንያ አትሌቲክስ የዓለም የ10 ሺህ ሜትር የነሐስ ሜዳሊያ አሸናፊዋ አግነስ ቲሮፕን ድንገተኛ ሞት ሲሰማ እጅጉን ደንግጧል" ብሏል።

ተቋሙ የአትሌቷን ሞት በተመለከተ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት እየሰራሁ ነው ብሏል።

" ኬንያ በዓለም መድረክ ከፈጣን ሯጮች አንዷ የነበረችውን ድንቅ አትሌት አጥታለች። በሩጫዋ ዐይንን በማያስከድነው ብቃቷ እናመሰግናታለን" ሲልም በአትሌቷ ሞት የተሰማውን ሀዘን ገልጿል።

ቲሮፕ ያስመዘገበቻቸው ዓለም አቀፍ ድሎች

ቲሮፕ በዓለም አቀፍ ደረጃ ድልን ያጣጣመችው እአአ በ2012 እና 2014 በዓለም ታዳጊዎች 5 ሺህ ሜትር የሩጫ ውድድር የነሃስ ሜዳሊያ በማግኘት እንዲሁም በ2013 በዓለም ታዳጊዎች አገር አቋራጭ ውድድር የብር ሜዳሊያ በማግኘት ነበር።

ከሁለት ዓመት በኋላ ደግሞ በቻይና በተካሄደው የዓለም አገር አቋራጭ ውድድር አሸናፊ መሆን ችላለች። ቲሮፕ በዚህ ውድድር በማሸነፍም ከደቡብ አፍሪካዊቷ መካከለኛ ርቀት ሯጭ ዞላ በድን ቀጥላ ሁለተኛዋ ወጣት ሴት መሆን ችላ ነበር።

ነሐሴ ወር ላይ በተካሄደው የቶክዮ ኦሊምፒክ ውድድሮች ቲሮፕ በሴቶች 5 ሺህ ሜትር ሩጫ ከኢትዮጵያዊቷ አትሌት ጉዳፍ ፀጋይ ጋር ብርቱ ፉክክር አድርጋ በ0.75 ሴኮንድ ልዩነት በአራተኛ ደረጃ አጠናቃለች።

የአትሌቷን ሞት ተከትሎም ፕሬዚደንት ኡሁሩ ኬንያታ " ወጣቷን፤ የ25 ዓመቷን የወደፊት ታላቅ አትሌት እና ለአገራችን በርካታ ድሎችን ያመጣችውን አትሌት ማጣታችን የሚረብሽ፣ እጅግ የሚያሳዝንም ነው። " ብለዋል።

"በሁሉም መልኩ ጀግና የሆነችው አትሌት ራስ ወዳድ እና ፈሪ በሆኑ ሰዎች የወንጀል ድርጊት የወጣትነት ዘመኗ መቀጨቱ በጣም ያማል" ብለዋል ፕሬዚደንቱ።

ፕሬዚደንቱ ሕግ አስፈጻሚ አካላት የቲሮፕ ግድያ ተጠያቂ የሆኑ ወንጀለኞችን አድነው በመያዝ ለሕግ እንዲያቀርቡ አሳስበዋል።