ባይደን 2500 ወታደሮችን በአፍጋኒስታን እንዲያቆዩ መምከራቸውን ጀነራሎች ተናገሩ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ሁለት የአሜሪካ ከፍተኛ ጀነራሎች አሜሪካ ነሐሴ ወር ላይ ጦሯን ከአፍጋኒስታን ሙሉ በሙሉ ከማስወጣቷ ቀደም ብሎ በአፍጋኒስታን 2500 ወታደሮችን እንዲያቆዩ ለፕሬዝደንት ባይደን ምክረ ሃሳብ ሰጥተው እንደነበረ ተናገሩ።
ጀነራል ማርክ ሚሌይ እና ጀነራል ፍራንክ ማክኬንዚ ለኮንግረንሱ የሰጡት ይህ ምስክርነት ግን ፕሬዚደንት ጆ ባይደን 'እንዲህ ዓይነት ምክር ሃሳብ መቅረቡን አላስታውስም' በማለት ከሰጡት አስተያየት ጋር የሚቃረን ይመስላል።
አሜሪካ ጦሯን ከአፍጋኒስታን ካወጣች በኋላ ታሊባን በፍጥነት የአገሪቷን ክፍሎች በመቆጣጠር ሥልጣን የያዘው ነሐሴ ወር ላይ ነበር።
ጀነራል ሚሌይ የአፍጋኒስታን መንግሥት በፍጥነት የወደቀበት ሁኔታ አሜሪካ ያልጠበቀችው ነበር ብለዋል።
ሁለቱ የአሜሪካ ጀነራሎች ከመከላከያ ዋና ኃላፊ ልሎይድ ኦስሊን ጋር በምክር ቤቱ የጦር አገልግሎት ኮሚቴ ማክሰኞ ዕለት ጥያቄ ቀርቦላቸው ነበር።
ይህ የሆነው የውጭ አገር መንግሥታት ዜጎቻቸውን ከአፍጋኒስታን ለማስወጣት እና በሺዎች የሚቆጠሩ ተስፋ የቆረጡ አፍጋናውያን ለመሰደድ ከካቡል አየር ማረፊያ ለመውጣት ትርምስ ከተፈጠረ ከሳምንታት በኋላ ነው።
ሰዎችን ከካቡል አየር ማረፊያ በማስወጣት ዘመቻ ወቅት በአጥፍቶ ጠፊ ጥቃት182 ሰዎች ተገድለዋል። 13 የአሜሪካ ወታደሮች እና ቢያንስ 169 አፍጋናውያን በአየር ማረፊያው በር ላይ የተገደሉት ነሐሴ 20 ነበር።
በአፍጋኒስታን ወታደሮችን ማቆየት
ወታደሮቹን የማስወጣት ሥራውን ሲከታተሉ የነበሩት የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ አዛዥ ጀነራል ማክኬንዚ ፕሬዝደንት ባይደን በአፍጋኒስታን 2500 ወታደሮች እንዲያቆዩ ሃሳብ ሰጥቼ ነበር ብለዋል።
ይሁን እንጂ ይህ የጀነራሉ ምስክርነት ጆ ባይደን ነሐሴ 19 ለኤቢሲ ጋዜጠኛ ከሰጡት ሃሳብ ጋር ይቃረናል። ባይደን በአፍጋኒስታን የተወሰኑ ወታደሮች እንዲቆዩ ሃሳብ ያቀረበ ሰው ስለመኖሩ እንደማያስታውሱ ተናግረው ነበር።
ጀነራል ሚሌይ በበኩላቸው 2500 ወታደሮችን በአፍጋኒስታን በማቆየት ሃሳብ መስማማታቸውን ገልጸው፤ የባይደን አስተያየት 'የሐሰት መግለጫ' መሆን አለመሆኑን በተመለከተ ላቀረበላቸው ጥያቄ ግን ቀጥተኛ መልስ ከመስጠት ተቆጥበዋል።
የጀነራሎቹን ምስክርነት ተከትሎ የዋይት ሃውስ ቃል አቀባይ ጀን ፕሳኪ ምላሽ ሰጥተዋል።
ቃል አቀባይዋ "ፕሬዚደንቱ ለጦሩ እና ለአዛዦቹ ሃሳብ ዋጋ ይሰጣሉ፤ ይህ ማለት ግን ሁል ጊዜ በዚህ ይስማማሉ ማለት አይደለም" ብለዋል።
ቃል አቀባይዋ አክለውም ከነሐሴው ቀነ ገደብ በኋላ በአፍጋኒስታን ወታደሮች ቢቀሩ ኖሮ አሁን ላይ አሜሪካ ከታሊባን ጋር ጦርነት ውስጥ ትሆን ነበር ብለዋል።












