ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ጀርመን ከአንጌላ ሜርክል በኋላ ማን እንደሚመራት በዛሬው ምርጫ ትወስናለች
ለረዥም ዓመታት ጀርመንን የመሯት መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ማን ይተካቸው ይሆን? የሚለው የጀርመኖች ጥያቄ በዛሬው እለት በሚደረገው ምርጫ ይመለሳል።
ጀርመናውያን በፓርላማ ምርጫ በበርካቶች ዘንድ እውቅናን ያተረፉትን ሜርክልን የሚተኩትን መሪያቸውን ይመርጣሉ።
የመዲናዋ በርሊን ጎዳናዎች ዓመታዊውን የማራቶን ውድድር እያስተናገዱ ቢሆንም ትልቁ ውድድር ግን በመላው አገሪቱ እየተካሄድ ያለው ምርጫ ነው።
በመራጮች ላይ የመጨረሻ ግፊት ለመፍጠር በሚመስል መልኩ ተሰናባቿ ቻንስለር ወግ አጥባቂውን አርሚን ላስቼትን አጅበው በትውልድ ከተማው አቼን ቅዳሜ እለት በተደረገው ሰልፍ ታይተዋል።
የድምፅ መስጫ አስተያየቶች እንደሚጠቁሙት ያልታሰበ ድል በእጃቸው ውስጥ ሊሆን ይችላል።
በአውሮፖ ውስጥ ኃያል የምትባለው የባለ 60 ሚሊዮን ህዝቦች ባለቤቷ ጀርመን በተወሰነ መልኩ ምጣኔ ኃብቷ አደጋ ውስጥ መግባቱም እየተነገረ ነው።
ይህንን የሚታደግ ቀጣዩ መሪን ለመምረጥ ከ18 አመት በላይ የሆኑ ጀርመናውያን በዛሬው ዕለት ደምፃቸውን ይሰጣሉ።
የምርጫ ጣቢያዎች በዛሬው ዕለር በአገሬው ሰዓት አቆጣጠር 2 ሰዓት ጥዋት ተከፍተዋል።
የድምጭ መስጫ ሰዓት በሚጠናቀቅበት 12 ሰዓትም ማን ነው ጀርመንን የሚመራትም ለሚለው ግልፅ አመላካች ይታያል።
ለዓመታት ጀርመንን የገዟት ሜርክል በአገራቸው የፖለቲካ ስፍራ ከፍተኛ ሚና ያላቸው ሲሆኑ በዘንድሮው ምርጫ እንደማይሳተፉ ያስታወቁት ከሶስት ዓመታት በፊት ነበር።
የስልጣን ዘመኔ ከተጠናቀቀ በኋላ ምንም አይነት ፖለቲካዊ አንቅስቃሴ አልፈልግም ሲሉም ተደምጠዋል።
" በእርግጥ ስልጣን ላይ የሚወጣው ማን ነው የሚለው ትልቅ ቦታ ልንሰጠው የሚገባ ነው" በማለት ድምፅ ከመሰጠቱ ከ48 ሰዓታት በፊት ቻንስለሯ አስጠንቅቀዋል።
ቻንስለሯ እንደሚያምኑት የጀርመንን መረጋጋት እንዲሁም የወጣቱን ወደፊት ብሩህ ሊያረግ የሚችለው ፖለቲከኛ አርሚን ላስቼት ነው።