ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ቢትኮይን ፡ በኤል ሳልቫዶር የቢትኮይንን ሕጋዊ መገበያያነት በመቃወም ሰልፍ ተደረገ
በላቲን አሜሪካዋ አገር ኤል ሳልቫዶር በሺዎች የሚቆጠሩ ተቃዋሚዎች መንግሥት ቢትኮይንን እንደ ሕጋዊ የመገበያያ ገንዘብ በመቀበሉ ቁጣቸውን ለመግለጽ አደባባይ ወጡ።
የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ናይብ ቡኬሌ ክሪፕቶከረንሲ በውጭ አገር የሚሰሩ ሳልቫዶራውያን ገንዘባቸውን በቀላሉ ወደ አገራቸው እንዲልኩ ይረዳቸዋል ብለዋል።
ሰልፈኞቹ ግን በከፋ ድህነት ውስጥ የምትገኘውን ኤል ሳልቫዶር ወደ በለጠ የዋጋ ግሽበት ብሎም ያለመረጋጋት ይወስዳታል ብለው ይሰጋሉ።
ከሰልፈኞቹ መካከል የተወሰኑት አንድ አዲስ የቢትኮይን ማሽን በእሳት ሲያቃጥሉ ሌሎች «ቡኬሌ አምባገነን» የሚል መፈክር ይዘው ታይተዋል።
ባሳለፍነው ሳምንት ኤል ሳልቫዶር ከአሜሪካ ዶላር በተጨማሪ ክርፒቶከረንሲን እንደ ሕጋዊ የመገበያያ ዘዴዋ በመጠቀም የመጀመሪያዋ አገር ሆናለች።
በዋና ከተማዋ ሳን ሳልቫዶር የተሰበሰቡት ሰልፈኞቹ ይህንን ሰልፍ ያካሄዱት አገራቸው 200ኛውን የነፃነት በዓሏን በምታከብርበት ቀን ነው።
« እምቢ ለቢትኮይን» እና «ሕገ -መንግሥቱ ይከበር» የሚሉ መፈክሮች በሰልፉ ላይ ከታዩት መካከል ናቸው።
ሰልፈኞቹ ፕሬዚዳንቱ ሥልጣናቸውን ተጠቅመው ቆይታቸውን ለማራዘም አቅደው ተንቀሳቅሰዋል ሲሉም ይከሳሉ።
ምንም እንኳን ሕገ-መንግሥታዊ ገደብ ቢቀመጥም ቡኬሌ ለሁለተኛ ተከታታይ ጊዜ ለፕሬዝደንትነት እንዲወዳደሩ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ፈቅዶላቸዋል።
«ዛሬ ማለዳ ማለት የምፈልገው ነገር ቢኖር- በቃ! ማለት ነው። መንግሥት እያደረገ ያለው እብሪተኛ እና አምባገነናዊ ተግባር ነው» ሲሉ አንድ በተቃውሞ ሰልፉ ላይ የተሳተፉ ግለሰብ ለሮይተርስ የዜና ወኪል ተናግረዋል።
ነገር ግን ፕሬዝደንት ቡኬሌ አሁንም በኤል ሳልቫዶር ጠንካራ ድጋፍ አላቸው።
በቅርቡ አንድ የአገር ውስጥ ጋዜጣ ባደረገው የሕዝብ አስተያየት ጥሪ 85.7% የሚሆኑ ድምጽ ሰጪዎች ለፕሬዝደንቱ ድጋፋቸውን ሰጥተዋል።